አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ― ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ገላን ኮንዶሚኒየም በመውሰድ የግድያ ቦታ አመቻችታለች ተብላ የተከሰሰችው ላምሮት ከማል ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ክርክር ለማድረግ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ተሰምቷል፡፡
ተለዋጭ ቀጠሮውን የሰጠው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው፡፡
በተከሳሿ ላይ ከአንድ ወር በፊት የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 2ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዓቃቤ ሕግ የቀረበ ማስረጃ ለወንጀሉ መፈፀም አስረጂ አደለም ሲል በነጻ አሰናብቷት የነበረ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ በብይኑ ቅር በመሰኘቱ ለጠቅላይ ይግባኝ አቅርቧል፡፡
ይግባኝ ሰሚ ችሎቱም ይግባኙ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን መርምሮ ያስቀርባል በማለት ለተከሳሿ ባለችበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መጥሪያ እንዲደርሳት ተደርጓል፡፡
በዛሬው ችሎት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመብራት ባለመኖሩና ተጠርጣሪዋ መጥሪያ ሲደርሳት እኔም በፕላዝማ ተገኝቼ ሐሳቤን ላቅርብ በማለቷና ተከላካይ ጠበቃዋም በችሎት መደራረብ ምክንያት ማረሚያ ቤት ሄጄ ደንበኛዬን ማግኘት አልቻልኩም በማለቱ ምክንያት ፍርድ ቤቱ የተከሳሿ ሀሳብ መደመጥ አለበት ሲል ለቃል ክርክር ለማድረግ ለሰኔ 9፣ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ ላምሮት ከማል ሰኔ 22፣ 2012 በአዲስ አበባ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ በሽጉጥ ተመቶ ሕይወቱ ያለፈውን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተገናኘ ከአንድ የሸኔ አመራር ጋር በሜክሲኮ አካባቢ በመገናኘት ተልኮ ተቀብላ ሃጫሉን ወንጀሉ ወደ ተፈፀመበት ቦታ በመውሰድ ግድያውን አመቻችታለች ተብላ መከሰሷ ይታወሳል፡፡