Sunday, September 22, 2024
spot_img

በምዕራብ ጉጂ ዞን የጸጥታ ኃላፊን ጨምሮ 7 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት አንድ የአካባቢው ባለሥልጣንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል፡፡

በምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት በዞኑ የሚገኘው ገላና ወረዳ የጸጥታና የደኅንነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ጃርሶ በካሎን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን የወረዳው የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ገበየሁ ያደቴ ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አቶ ገበየሁ እንዳሉት ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 14፣ 2013 ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ በጥቃቱ ሁለት የሚሊሻ አባላት፣ ሦስት የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት፣ የወረዳው ጸጥታና ደኅንነት ኃላፊና እና የጽህፈት ቤቱ የደኅንነት ባለሙያ ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።

ከደቡብ ክልል የአማሮ ወረዳ ጋር በሚዋሰነው በዚህ አካባቢ እንዲህ ያለው ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ በፊትም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ግድያዎች መፈጸማቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ባለፈው መጋቢት ወር ሁለቱ ወረዳዎች በሚያዋሰኑበት ሥፍራ ስብሰባ ላይ በነበሩ አመራሮችና ነዋሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ስድስት ደግሞ ቆስለው ነበር።

በወቅቱ ጥቃቱን የፈጸሙት መንግሥት ‹ሸኔ› ብሎ የሚጠራውና እራሳቸውን ‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት› የሚሉት ታጣቂዎች እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፤ አሁንም ለሰባት ሰዎች ህልፈት ምክንያት ለሆነው ጥቃት ይኸው ታጣቂ ቡድን በተጠያቂነት ይከሰሳል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img