Sunday, September 22, 2024
spot_img

ዓቃቤ ሕግ ኤፈርት ከሕወሓት ጋር ያለውን ግንኙነት እያጣራሁ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ግንቦት 8፣ 2013 ― የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኤፈርት የተባለውን ኩባንያ ባለቤትነት፣ ከሳምንት በፊት በአሸባሪነት ከተሰየመው ሕወሓት ጋር ግንኙነት እንዳለውና እንደሌለው እያጣራ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የመስፍን ኢንዱስትሪያል የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ፣ ጉና የንግድ ሥራዎች ኩባንያ፣ ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ ትራንስ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶችን በውስጡ አቅፎ የያዘው ኤፈርት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በንግድ ሥራ መሰማራቱ ይታወቃል፡፡

በታኅሳስ 2013 ኤፈርት በጥቂት የሕወሓት አባላት ተይዞ እንደነበር በመጥቀስ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳር ከፍተኛ አመራሮች በሥሩ ያሉ ድርጅቶች በባለአደራ እንዲመሩ በማድረግ ለፍርድ ቤት ውሳኔ ማቅረቡን፣ የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ አመራርና የአሁኑ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት ለጋዜጠኞች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በ2012 የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176፣ አንድ በአሸባሪነት የተሰየመ ድርጅት ንብረት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደሚወረስ ይደነግጋል፡፡

በርካታ ግዙፍ የንግድ ተቋማትን በአንድ ጥላ ሥር የያዘውን ኤፈርት ያንቀሳቅሳል የሚባልለት ሕወሓት፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅራቢነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት እንዲሰየም በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁ ይታወሳል፡፡

የፌዴራል ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋ ኩባንያው አሁን ንብረትነቱ የማን እንደሆነ ለማጣራት በዓቃቤ ሕግ የሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር በኩል የምርመራ ሥራ እየተካሄደበት መሆኑን ነግረውኛል ብሎ ሪፖርተር ዘግቧል።

‹‹ተቋሙ የሕወሓት ከሆነ ይወረሳል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የኢፈርትን የባለቤትነት ጥያቄ ይህ ነው ብሎ መመለስ አይቻልም፤›› ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ገልጸዋል፡፡

ምርመራው ተጠናቆ ይወረስ ከተባለ ቀጥታ አዋጁ በተጠቀሰበት አግባብ እንዳለ የሚወረስ ሳይሆን፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉን ተከትሎ በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎበት የክልሉ ሀብት ሊሆን እንደሚችል አክለው ተናግረዋል፡፡

በኅዳር 2013 ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕወሓት የንግድ ድርጅቶች ናቸው የተባሉ 34 የንግድ ተቋማት፣ የባንክ ሒሳባቸው ዕግድ እንዲጣልባቸው ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡

ዕግዱ የተጣለባቸው የምርትና የንግድ ተቋማት ሲሆኑ በፋይናንስ፣ በማዕድን፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በግንባታ፣ በጅምላ ንግድ፣ በትራንስፖርት፣ በፋብሪካ ምርቶችና በመሳሰሉት የተሰማሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከሕወሓት ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳላቸው ተገልጾ ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img