Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሕወሓትን ትጥቅ የማስፈታት ሒደት ሲጠናቀቅ የሽብርተኝነት ፍረጃው ተነስቶ የመሪዎቹ ክስ ይቋረጣል ተባለ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ታኅሣሥ 26 2015 ― በጥቅምት ወር መገባደጃ በደቡብ አፍሪካ በተደረሰው የመንግሥት እና ሕወሓት የሰላም ስምምነት መሠረት የሕወሓት ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የማስፈታት ሒደቱ ከጫፍ ሲደርስ፣ በሕወሓት ላይ የተጣለው የሽብርኝነት ፍረጃ እንደሚነሳ እና በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተከፈተው የወንጀል ክስም እንደሚቋረጥ ተነግሯል፡፡

በ2013 ጥቅምት ወር ላይ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ መመታቱን ተከትሎ ከተነሳው ጦርነት ጋር በተገናኘ ከመንግሥት ጋር ጦርነት የገጠመው ሕወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት እንደተፈረጀ ይታወቃል፡፡ ጦርነቱ በአፍሪካ ህብረት ዋና አደራዳሪነት ሲቆም መንግሥት እና ሕወሓት ካደረጓቸው ስምምነቶች መካከል የሕወሓት ትጥቅ መፍታት ዋንኛው ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥቱም ትግራይን ተቆጣጥሮ በሽብር በሰየመው ሕወሓት ምትክ አዲስ አስተዳደር እንደሚተካ ተቀምጧል፡፡

ከስምምነቱ በኋላ ከአስር ቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታፈሰ ጫፎ የተመራ ልኡክ መቐለ በማቅናት ከክልሉ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ከስምምነቱ በኋላ በትግራይ መሠራታዊ አገልግሎተች የተመለሱ ሲሆን፣ በቀጣይ መንግሥት በሕወሓት ላይ የጣለውን የሽብርተኝነት ፍረጃ አንስቶ በመሪዎቹላይ የተጣለውን ክስ እንደሚያቋርጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸውን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡

ይህንኑ ለምክር ቤቱ ዓርብ ታኅሳስ 21፣ 2015 የተናገሩት ሬድዋን፤ ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው የሕወሓት ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የማስፈታት ሒደቱ ከጫፍ ሲደርስ መሆኑን ጠቁመዋል ነው የተባለው፡፡

አማካሪ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት በተመሳሳይ ‹‹የትጥቅ መፍታት ሒደቱ ጫፍ ሲደርስ ለፖለቲካ ሒደቱ በር መክፈት ስለሚያስፈልግ፣ ፓርላማው የሽብር ፍረጃውን ሊያነሳ ይችላል። የተመሠረተ የወንጀል ክስ ሒደትም እንዲቋረጥ የሚደረግበት ሁኔታ ይኖራል›› ብለው ነበር።

ይህ የሚደረገው ሰላም ለማምጣት ሲባል እንደሆነ የተናገሩት ሬድዋን፣ ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀና የወንጀል ክስ ከተመሠረተበት አካል ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር ስለማይቻል፣ ክስ መቋረጥና የሽብርተኝነት ፍረጃው መነሳት እንዳለበት ገልጸዋል። ‹‹ሰላም ለማምጣት አንዳንድ መራራ አካሄዶች ይኖራሉ። ይህም ሰላምን ለማምጣት የሚከፈል ዋጋ ነው›› ብለዋል።

ሕወሓት በአሁኑ ወቅት ከባድ የጦር መሣሪያዎቹን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያስረከበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመከላከያ ሠራዊቱ አንድ ሻለቃ ጦር ከባድ መሣሪያውን ተረክቦ በጥበቃ ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከሰሞኑ ለሚዲያዎች መግለጻቸው ይታወቃል።

ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም ለማስከበርና የፌዴራል ተቋማትን ለመጠበቅ መሰማራታቸውም ተገልጿል። በአሁኑ ወቅትም የፌዴራል ፖሊስ ከመቀሌ ከተማ በተጨማሪ፣ በአዲግራትና በተከዜ አካባቢዎች፣ እንዲሁም ከማይጨው እስከ መቀሌ ባሉ ከተሞች እንደተሰማራ ታውቋል። 

ሬድዋን (አምባሳደር) ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት፣ የፀጥታን ማረጋገጥ ሥራ ከሕወሓት ጋር በጋራ የሚሠራ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፣ ለዚህም ከሕወሓት በኩል ለፀጥታ ሥራ የተመረጡና የሠለጠኑ ኃይሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስረድተው ነበር።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img