Saturday, May 18, 2024
spot_img

ወደ መቐለ ከተማ ያቀኑት የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ያለ ግል ጠባቂዎቻቸው ትግራይ መግባታቸው ተገለጸ

  • የሕወሓት ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አመስግነዋል
  • የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በመቐለ ሰማይ ሲያንዣብብ በመቐለ ሕዝብ እልልታ መታጀቡ ተነግሯል

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ ታኅሣሥ 18 2015 ― ትላንት ሰኞ ታኅሣሥ 17፣ 2015 ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ ያቀኑት የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ያለ ግል ጠባቂዎቻቸው ትግራይ ክልል መግባታቸውን የገለጹት የሕወሓት አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው፡፡ አቶ ጌታቸው ይህን የተናገሩት የባለሥልጣናቱን የመቐለ ጉብኝት በተመለከተ ለመንግሥት እና ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ የመሩት የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን የያዘው ከፍተኛ ልዑክ፤ ትላንት ረፋድ ወደ መቐለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ሲደርስ፤ በመንግሥት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል ከተካሄደው ሁለት ዓመት የዘለቀ ጦርነት በኋላ የመጀመሪያው ሆኗል፡፡

ልዑኩ መቐለ ሲደርስ የሕወሓት ባለሥልጣናት እና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በበርካታ ሰዎች አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ልዑኩን በዋነኝነት የሕወሓት አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ሲቀበሉ ታይተዋል፡፡ ከፌዴራል መንግሥቱ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ሬድዋን ሑሴን፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታዋ ሠላማዊት ካሣ፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት አማረ እንዲሁም ሌሎችም ተካተዋል፡፡

ልዑኩን በተመለከተ የተናገሩት የሕወሓቱ ሰው ጌታቸው ከባለሥልጣናቱ መካከል እስከ ስድስት የካቢኔ አባላት እንዳሉበት አስታውሰው፤ ሆኖም እነዚህ ባለሥልጣናት ያለ ጠባቂ መቐለ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ ይህን ማድረጋቸው በአንድ በኩል ‹‹በትግራይ መንግሥትም ሕዝብም በኩል ለሠላም ያለውን ቁርጠኝነት መገንዘባቸውን ያመለክታል›› ያሉት ጌታቸው፤ በሁለተኛ ደረጃ ‹‹ሠላማዊ መፍትሔው ጫፍ እንዲደርስ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን›› አመልካች ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣናቱ ወደ መቐለ ከተማ ያለ ጠባቂ ገብተዋል መባሉን በተመለከተ ከፌዴራል መንግሥቱ በኩል አስተያየት አልተሰጠበትም፡፡

የትላንትናው የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ወደ መቐለ ማቅናት በአዲስ አበባ እና መቐለ በበርካቶች ዘንድ የተለያ ስሜት ፈጥሯል፡፡ በሕወሓት በሚተዳደረው የትግራይ ቴሌቪዥን የምትሠራው ጋዜጠኛ መድኅን ገ/ሥላሴ የመቐለ ከተማ ሕዝብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በከተማው ሰማይ ሲመለከት በደስታ እልልታ ማሰማቱን ጽፋለች፡፡

በፌዴራል መንግሥት ሰዎች የመቐለ ከተማ ጉብኝት ባለሥልጣናቱ ከሕወሓት ሰዎች ጋር ውይይት አድርገው በመጨረሻ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ወቅት የሕወሓት ሊቀመንበር ከሠላም ስምምነቱ በኋላ ያሉ ሁኔታዎችን አብራርተዋል፡፡ በዚህ ማብራሪያቸው ለሠላም ስምምነቱ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ ሲሉ የተደመጡት ደብረጽዮን፤ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አመስግነዋል፡፡  ደብረጽዮን በንንግራቸው ‹‹የሠላም ጉዞውን ጀምረነዋል፡፡ የዛሬው ግን የተለየ ነው፡፡ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ዐቢይን ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ማመስገን አፈልጋለሁ›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ዶክተር ደብረጽዮን በሰጡት መግለጫ፤ የሠላም ስምምነቱ ላይ የሠፈረውን የሕወሓት ትጥቅ መፍታት ጉዳይ አንስተዋል፡፡ በዚህ ማብራሪያቸው በስምምነቱ መሠረት የሕወሓት ኃይሎች ከነበሩባቸው አራት ግንባሮች ለቅቀው መውጣታቸውን ጠቁመው፤ ሆኖም የኤርትራ ጦር ባለባቸው ቦታዎች ግን አሁንም ጦራቸው እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የመሠረታዊ አገልገሎቶች መመለስ ጉዳይም የሕወሓት ሊቀመንበር መግለጫ አካል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የኤሌክትሪክ፣ ባንክ እና በረራዎችን በተመለከተ ያነሱት ደብረጽዮን፤ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናን ይዞ መቐለ የገባው አውሮፕላን ሲቪሎችን ሲያመላልስ መመልከት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ማክሰኞ ታኅሣሥ 18 ማለዳ ከነገ ረቡዕ ጀምሮ ወደ መቐለ በረራ እደሚጀምር አስታውቋል፡፡

በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል ጥቅምት 24፣ 2013 የጀመረው ጦርነት፤ በዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተቋጨው ጥቅምት 23፣ 2015 እንደነበር ይታወቃል፡፡ ደም አፋሳሹ ጦርነት በመቶ ሺሕዎች ሲቀጥፍ፤ ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img