Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሕወሓት ከመንግሥት ጋር ተደራዳሪዎችን ለመሠየም መዘጋጀቱን ገለጸ

አምባ ዲጂታል፤ ሰኞ ሐምሌ 11 2014 ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለ20 ወራት የዘለቀ ጦርነት ውስጥ የገባው ሕወሓት፤ ጉዳዩን በሰላም ለመቋጨት ከመንግሥት ጋር ተደራዳሪዎችን ለመሠየም ዝግጁ መሆኑን ያስታወቁት የፓርቲው ሰው ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ናቸው፡፡

የሕወሓት ተደራዳሪዎች ይፋ መደረግ ጉዳይ የመጣው ባለፈው ሳምንት መንግሥት የሰየማቸው የሰላም ተደራዳሪዎች ሥራ መጀመራቸውን ማሳወቁን ተከትሎ ነው፡፡

የቡድኑን ሥራ መጀመር ይፋ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፤ እርሳቸው አባል የሆኑበት የመንግሥት ተደራዳሪ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ለሚካሄደው ንግግር የራሱን አካሄድ ተወያይቶ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

የሕወሓቱ ተወካይ ፕሮፌሰር ክንደያ ግን ቡድናቸው ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚያካሄደው የሰላም ንግግር በማን አደራዳሪነት እንደሚካሄድ የገለጹት ነገር የለም፡፡ ሆኖም ሕወሓት ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ አዲስ አበባ እና መቐለ ሲመላለሱ በቆዩት በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ላይ ያለውን እምነት አናሳ መሆኑን በመጠቆም፤ በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪነት ለሚደረግ ንግግር ዝግጁ መሆኑን አሳውቆ ነበር፡፡ ሕወሓት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ከዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር ቅርበት አላቸው ሲልም በመግለጫው አስፍሯል፡፡

ይህ በእንዲህ ባለበት የሕወሓት ተወካዩ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት የፌዴራሉን መንግስት አንድ ጊዜ የሰላም ምልክት ያሳያል ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠብ ይደግሳል ሲሉ መወንጀላቸውን ሱዳን ትሪቡን አስነብቧል፡፡ በምሳሌነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር ያነሱት ክንደያ፤ ስለ ሰላም በተናገሩበት ቅጽበት በአገሪቱ ላሉ ችግሮች ሁሉ ሕወሓትን ተጠያቂ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

አያይዘውም ይህንኑ በመንግሥት ሚዲያዎች ማስተዋል እንደሚቻል የገለጹ ሲሆን፣ ከፌዴራል መንግሥቱ በኩል የምር ሰላም ከተፈለገ ንጹህ ሆኖ መምጣት ይገባል ብለዋል፡፡

ያለፉትን ሃያ ወራት በጦርነት ውስጥ የቆዩት የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ከዚህ ቀደም በታንዛንያ አሩሻ ተደራዳሪዎቻቸው ይገናኛሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ሁለቱ አካላት አሁንም ድረስ የት እንደሚደራደሩ የተነገረ ነገር የለም፡፡

የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ያደረጉት ጦርነት ለበርካታ ሺሕዎች ሕይወት መቀጠፍ ሰበብ ሲሆን፤ የጦርነቱ መነሻ በነበረው ትግራይ እንዲሁም አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img