Friday, November 22, 2024
spot_img

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የአሜሪካ ወታደሮች ዳግም በሶማሊያ እንዲሰማሩ ባይደን የሰጡትን ትዕዛዝ መቀበላቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 9 2014 አሜሪካ በፕሬዝዳንትዋ ጆ ባይደን በኩል የአገሪቱ ወታደሮች ዳግም በሶማሊያ እንዲሰማሩ በትላንትናው እለት ትዕዛዝ ሰጥታለች፡፡

አገሪቱ ከዚህ ቀደም ወታደሮቿን በሶማሊያ ያሠማራችው የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ሠራዊትን በማደራጀት፣ በማሠልጠን እና ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ለማማከር በሚል ነበር፡፡

ነገር ግን ከባይደን በፊት የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ ቀደም ሲል ተሰማርተው የነበሩ የአሜሪካ ወታደሮችን ከአገሪቱ ጠቅልለው እንዲወጡ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡

የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሶማሊያ እሑድ እለት አዲስ ፕሬዝዳንት መምረጧን ተከትሎ የአገራቸው ወታደሮች እንደገና በሶማሊያ እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጥተው የነበረ ሲሆን፣ ይህንኑ ትዕዛዝ 10ኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ በደስታ እንደሚቀበሉት መግለጻቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

አሜሪካ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገዛዝ ዘመን ከሶማሊያ ያስወጣቻቸው ወታደሮች ብዛት 700 ያህል ነው፡፡ አሜሪካ ወታደሮችን ከሶማሊያ ብታስወጣም፣ ፔንታጎን ግን እዋጋዋለሁ በምትለው አልሸባብ ዒላማዎች ላይ የድሮን ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

አሁን በባይደን ትእዛዝ የተሰጠበትና በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ተቀባይነት ባገኘው እቅድ መሠረት አሜሪካ ወደ ሶማሊያ የምታሠማራቸው ወታደሮች ብዛት ከ500 እንደሚበልጥ ተነግሯል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img