አምባ ዲጂታል፤ ቅዳሜ ጥቅምት 03፣ 2016 – የመንግሥት ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ የገንዘብ ምንዛሬ በገበያ ብቻ እንዲወሰን ለማድረግ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል ያሉት የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ናቸው፡፡
ምክትል ዳይሬክተሯ አናሊዛ ፌዴሊኖ ይህንኑ ለጋዜጠኞች የተናገሩት በሞሮኮ ማራካሽ አይኤምኤፍ ከዓለም ባንክ ጋር ባካሄዱት ጉባኤ ነው፡፡
አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተስማምተውበታል የተባለው የኢትዮጵያ የገንዘብ ምንዛሬ በገበያ ብቻ እንዲወሰን የማድረግ ጥያቄ የዓለም ገንዘብ ድርጅት በተደጋጋሚ ሲያነሳው የቆየ ነው፡፡ የዓለም ገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ሕጋዊውን የምንዛሬ ገበያና የትይዩ ገበያ አንድ ለማድረግ የብርን የመግዛት አቅም አሁን ካለበት ቢያንስ በእጥፍ በማውረድ የጥቁር ገበያው አሁን ካለበት እኩል ማድረግ ግዴታ መሆኑን ሲወተውቱ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለተኛው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ዶክመንት የምንዛሬ ገበያው ቀስ በቀስ መከፈቱ (Liberalize መደረግ) እንዳለበት ይጠቁማል፡፡
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት መንግሥት ይህን ቢሉም፤ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች በአንጻሩ ይህ ውሳኔ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ ቢችልም፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ ግን የገቢ ምርቶችን ማስወደድና በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ መናር ማባባስ ነው ይላሉ፡፡
የዓለም ገንዘብ ድርጅት ልዑካን ቡድን በቀጣይ ሳምንታት ቢያንስ አንድ ጊዜ ለድርድር ወደ ኢትዮጵያ ሊሄድ እንደሚችልም ተሰምቷል፡፡