አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ግንቦት 9፣ 2015 – የኦሮሚያ ክልላዊ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚያስገነባውን የክልሉን ፕሬዝዳንት መቀመጫ ሕንጻ ግንባታ በዛሬው እለት በይፋ አስጀምሯል።
በከተማዋ የሚገነባው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት መቀመጫ ከ6 ሔክታር በላይ በሆነ ቦታ ላይ የሚገነባ ነው። እንደ ክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ከሆነ የሚገነባው ሕንጻ በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል።
ግንባታውን የሚሰራው የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ሕንጻው ምን ያህል ገንዘብ እንደሚፈጅ ግን የተገለፀ ነገር የለም።
በዛሬው የሕንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ሕንጻውን የሚያስገነባው የኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት፣ አባ ገዳዎች እንዲሁም ሃዸ ሲንቄዎች ተገኝተዋል።