Sunday, September 22, 2024
spot_img

የፌደራል መንግሥት እና ሕወሓት ግጭት ከምን ተነስቶ የት ደረሰ?

ባለፉት አራት ዓመታት በተለይ ደግሞ ያለፉትን ሁለት ገደማ ዓመታት የቀድሞው የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ መሪ ሕወሓት እና አሁን በብልጽግና ፓርቲ የሚመራወ የፌዴራል መንግሥት የገቡበት ግጭት ኢትዮጵያውያንን በአንድም በሌላ መንገድ የነካ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ለመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ እና ሕወሓት ያሳለፏቸው አንኳር ሒደቶች ምን መሳይ ነበሩ?

ጥቅምት 14 2013 የፌዴራል መንግሥት ወታደራዊ የሥልጣን ሹም ሽር ሊያደርግ ነው መባሉን ተከትሎ የትግራይ ክልል ማዕከላዊው መንግሥት ይህን ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን የለውም አለ።

ጥቅምት 18 2013 ሕወሓት አንድ ነባር ወታደራዊ መኮንን ወደ መቐለ እንዳይገቡ አገደ። በተጨማሪም የሰሜን ዕዝን ለመምራት አዲስ የተሾሙት ሜጀር ጄነራል በላይ ስዩም ወደ ክልሉ መግባት እንደማይችሉ አሳወቀ።

ጥቅምት 22 2013 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕወሓትን ርምጃ ተከትሎ መሰል እንቅስቃሴዎችን እንደማይታገስ አስታወቀ።

ጥቅምት 24፣ 2013 ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ‹‹ከሐዲ ኢትዮጵያውያን፤ ኢትዮጵያን ወግተዋታል›› ሲሉ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ተናገሩ፡፡ አክለውም የአገር መከላከያ ሠራዊት መለዮውን፣ አገሩን እና ሕዝቡን እንዲከላከል ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጥቅምት 25 2013 የሕወሓት አመራር አባሉ ሴኩ ቱሬ ጌታቸው በድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን በቀረበ መሰናዶ የሰሜን እዝ ላይ ‹‹በጣም ፈጣን እና መብረቃዊ የሆነ እርምጃ›› ተወስዷል ሲሉ ተናገሩ

ኅዳር 4፣ 2013 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ላይ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ከደነገገ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ዶክተር ሙሉ ነጋን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ሾሙ፡፡

ኅዳር 19፣ 2013 ይፋዊ ጦርነት ቀጥሎ መከላከያ መቐለ ከተማን መቆጣጠሩን አስታወቀ፡፡

ጥር 10፣ 2013 ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕወሓት ‹‹ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር›› ላይ በመሳተፉ ሕጋዊ ሰውነቱን ሰረዘ፡፡

ሰኔ 21፣ 2013 የሕወሓት ኃይሎች የክልሉን መቐለን መቆጣጠራቸውን ሲያሳውቁ፤ መንግሥት ‹በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጥያቄ› መከላከያ መቐለን ለቆ መውጣቱን ገለጸ፡፡

ሐምሌ 2014 የሕወሓት ኃይሎች ጥቃታቸውን ወደ አማራ እና አፋር ክልል ከተሞች መሰንዘራቸው ተነገረ፡፡

ጥቅምት 20፣ 2014 ሕወሓት ደሴን ይዣለሁ ቢልም መንግሥት ከተማዋ አሁንም በቁጥጥሬ ስር ናት ሲል አሳወቀ፡፡

ጥቅምት 22 2014 የሕወሓት ኃይሎች በርካታ የአማራ ክልል ከተሞችን ተቆጣጥረው ኮምቦልቻ በመድረስ ‹‹ከ100 በላይ የከተማዋን ወጣቶችን አሰልፎ ጨፍጭፏል›› ሲሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጥቅምት 22 2014 ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ ‹የክት› ጉዳዩን አቆይቶ ሕወሓትን ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ማናቸውንም መሳሪያ እና አቅም ይዞ በሕጋዊ አደረጃጀት መዝመት አለበት ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።

ኅዳር 13፣ 2014 የሕወሓት ኃይሎች በርካታ የአማራ ክልል ከተሞችን አልፈው ወደ ሰሜን ሸዋ እየተቃረቡ መሆናቸው ሲነገር ‹‹ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ›› አሉ፡፡

ታኅሣሥ 2014 በጠ/ሚ ዐቢይ የተመራው መከላከያ ደሴ እና ኮምቦልቻን ነጻ ማውጣቱን መንግሥት ገለጸ፡፡

ታኅሣሥ 14፣ 2014 መከላከያ ከሕወሓት ኃይሎች ነጻ በማውጣት በቁጥጥሩ ስር ባስገባቸው የአፋርና የአማራ ክልል ቦታዎች ላይ እንዲቆይ መታዘዙ ተገለፀ።

መጋቢት 15፣ 2014 መንግሥት ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ሲያሳውቅ ሕወሓትም ተመሳሳይ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ሐምሌ ሐምሌ 21 2014 የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ እደራደራለሁ አለ፡፡

ነሐሴ 2014 የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት ባለሥልጣናት በምሥጢር በአካል ተገናኝተው እንደነበር የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

ነሐሴ 18 2014 ሕወሓት በጌታቸው ረዳ በኩል የፌዴራል መንግሥት ሌሊት 11 ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍቶብኛል አለ፡፡

ነሐሴ 18 2014 የፌዴራል መንግሥት ሕወሓት ጥቃት ሰንዝሮ የተኩስ ማቆሙን በይፋ አፍርሶታል አለ፡፡

መስከረም 24፣ 2015 የአፍሪካ ኅብረት መንግስት እና ሕወሓትን በደቡብ አፍሪካ ለማሸማገል ጥሪ አቀረበ፡፡

መስከረም 25፣ 2015 የፌዴራል መንግስት የአፍሪካ ኅብረትን ጥሪ ተቀበለ፡፡

መስከረም 25፣ 2015 የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የአፍሪካ ኅብረትን ጥሪ መቀበላቸውን ገለጹ፡፡

መስከረም 26፣ 2015 የአፍሪካ ኅብረት በደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን የመንግስት እና ሕወሓት ሽምግልና የሚመሩት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ መሆናቨቸውን ገለጸ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img