Saturday, May 18, 2024
spot_img

ከአስተዳደር ወሰን ማካለል ጋር በተገናኘ የሚፈጸሙ ውሳኔዎች አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ታሳቢ ያላደረጉ መሆኑን ኢዜማ አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ ነሐሴ 5 2014 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከአስተዳደር ወሰን ማካለል ጋር በተገናኘ ከአስተዳደር ወሰን ማካለል ጋር በተገናኘ የሚፈጸሙ ውሳኔዎች አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ታሳቢ ያላደረጉ መሆናችን ያሳወቀው ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ነው፡፡

ፓርቲው ዛሬ ነሐሴ 5፣ 2014 ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ፤ ሕዝብ የአስተዳደር ውሳኔን የመቀበል ግዴታ የሚኖርበት እንደ ዜጋ ሂደቱ ላይ የመሳተፍ እና የማወቅ መብቱ በአግባቡ ሲከበርለት ብቻ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ ኢዜማ ውሳኔዎችን በኃይል ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሊታወቅ ይገባል ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደር ወሰንን ጋር ተያይዞ ነው፡፡

የኢዜማ መግለጫ መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የአስተዳደር ወሰን ማካለሉ ‹‹ጠቃሚ መሆኑ ባይካድም›› ውሳኔዎቹን ማስተግበር የሚቻለው ‹‹ዜጎችን አሳትፎ የሂደቱ ባለቤት በማድረግ እንጂ በኃይል ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሊታወቅ ይገባል›› ብሏል፡፡

ኢዜማ እንደ ፓርቲ ከአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ወሰን ጋር በተገናኘ ዝርዝሩን በጥልቀት እንደሚጣራ የገለጸ ሲሆን፣ የአስተዳደር ወሰን ማካለል እና የክላስተር ውሳኔዎችን አገራዊ ምክክሩ ይፈታቸዋል በሚል ታሳቢ ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

አያይዞም ጉዳዩን የምናየው ‹‹ማን ምን አገኘ? ማንስ ምን አጣ?›› በሚል ቁንጽል እሳቤ ሳይሆን ከአግባብነቱ እና ጊዜውን ካለመጠበቁ አንፃር ‹‹ከፍተኛ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል›› ያለው የኢዜማ መግለጫ፤ ጉዳዩን በፍጥነት ሊታረም እንደሚገባም አሳስቧል፡፡  

ኢዜማ በአካባቢው እየኖረ ያለው ሕዝብ የመንግሥትን ውሳኔዎች የመቀበል ግዴታ የሚኖርበት እንደ ዜጋ ሂደቱን የማወቅ እና የመሳተፍ መብቱ ሲከበርለት ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ነው ያለው፡፡

ፓርቲው አዲስ አበባ ላይ እየተስተዋሉ ያሉ የአስተዳደር መደበላለቅ ችግሮችን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ሰብስቦ በጥናት የሚለይ ቡድን አቋቁሞ ቀደም ብሎ ሥራዎችን እንደጀመረ በማስታወስ፤ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡

ከአሁን በፊት ለከረረ ፓለቲካዊ ውዝግብና ተቃውሞ ምክንያት የነበረው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን አዲስ በተዘጋጀ ጥናት መሰረት የማካለል እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

የወሰን ማካለሉ በሁሉም የአዲስ አበባ ዙሪያ ወረዳዎችና በኦሮሚያ ክልል ስር ባሉ ልዩ ዞኖች መካከል የሚደረግ ሲሆን እንደየአካባቢው ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ አልያም ከኦሮሚያ ወደ አዲስ አበባ የሚካለሉ አካባቢዎች ተለይተዋል ነው የተባለው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img