አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ሐምሌ 27፣ 2014 ― የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፤ የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓትን ሽምግልናቸውን አስመልክቶ ነገ ሐሙስ ሐምሌ 28፣ 2014 ገለጻ የሚያደርጉት ለአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ነገ በሚካሄደው ስብሰባ በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሁኔታ ላይ የሚቀርበውን ገለጻ ያደምጣሉ ተብሎ ተጠብቋል፡፡ ኦባሳንጆም በዚሁ ስብሰባ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ለምክር ቤቱ ገለጻ ካደረጉ ወዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ያስረዳሉ ተብሏል፡፡
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ተደርገው ከተሾሙበት ነሐሴ 2013 አንስቶ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተፋላሚዎች መካከል የሰላም ንግግር ለማስጀምር አዲስ አበባ እና መቐለ ከተሞች ሲመላለሱ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በቅርብ ጊዜያት ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ድርድር ለማድረግ የተስማሙ ቢሆንም፤ አደራዳሪው ማን ይሁን በሚለው ግን የፌዴራል መንግስቱ በአፍሪካ ኅብረት ማእቀፍ ስር የሚለውን ሲመርጥ፤ ሕወሓት በበኩሉ በህብረቱ ተወካይ ኦባሳንጆ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ገልጾ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ ባለበት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደሮች ጋር በተገናኙበት ወቅት መንግሥት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ውይይቱን ተከትሎ በትዊተር ባሰፈሩት መልእክት፤ መንግሥት የአምባሳደሮቹ እና የልዩ መልዕክተኞቹ ቡድን ወደ መቐለ እንዲጓዝ መፍቀዱንም አመልክተዋል።
ይህንኑ ተከትሎ ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 26 የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር እና የአሜሪካ አቻቸው ማይክ ሐመር የተካተቱበት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስብስብ ወደ መቐለ አቅንቶ ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተወያይቷል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ይህ ስብስብ ከዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በትግራይ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ወደ ክልሉ ማቅናት ለሚፈልጉ አካላት የደህንነት ዋስትና የሚሰጥ ደብዳቤ ለፌደራል መንግስት ይዘው ተመልሰዋል፡፡
ደብረጽዮን ደብዳቤ መላካቸውን ያረጋገጠው የአውሮፓ ኅብረት፤ ተወካዩ አኔት ዌበር እና የአሜሪካው ማይክ ሐመር በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ‹‹ከጥላቻ ንግግር እና ጠብ ጫሪ መግለጫዎች›› እንዲቆጠቡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ገልጧል፡፡ ከደብዳቤው መላክ በኋላ ከፌዴራል መንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ ስለመኖሩ ተገለጸ ነገር የለም፡፡