Thursday, December 5, 2024
spot_img

ፖሊስ ጋዜጠኛ ያየሰው ሺመልስን ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በመሥራት ጠርጥሮ እንደያዘው ለፍርድ ቤት ገለጸ

  • ጋዜጠኛው በአሁኑ ጊዜ ሥራ እንደሌለው ለችሎት ተናግሯል

አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ ግንቦት 19 2014 ትላንት ግንቦት 18፣ 2014 በመኖሪያ ቤቱ በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ ያየሰው ሺመልስ በዛሬው እለት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቧል፡፡

በችሎቱ መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኛውን በዩትዩብ ‹‹ኢትዮ ፎረም›› በተሰኘ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሠራ በመጠቆም፤ በሀገሪቱ ተደራጅተው በስውር የኢኮኖሚ እና የሚዲያ ጦርነት የከፈቱ አካላት እንዳሉ የገለጸ ሲሆን፣ ያየሰው ብሔርን ከብሔር እና በሀይማኖትን ከሀይማኖት እንዲጋጭ እንዲሁም የፌደራል መንግስት እና ህዝብ ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ሚዲያን በመጠቀም ከሚሠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው ብሎታል፡፡

ለዚህ ምስክር መኖሩን የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ፤ የምስክር ቃል ለመቀበል ለብሔራዊ መረጃ ደህንነት ከተጠርጣሪው የተያዘ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለማስመርመር፣ ተጠርጣሪውን በምስክር ለማስመረጥ እንዲሁም ተጨማሪ ማስረጃ አሰባስቦ ለመቅረብ ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ጋዜጠኛ ያየሰው ሺመልስ በበኩሉ በአሁን ጊዜ ሥራ እንደሌለው ገልጾ፣ ፖሊስ ይህን ሲሠራ ይዤዋለው ካለ በየትኛው ሚዲያ፣ መቼ እና ምን የሚለውን በግልጽ ሊያቀርብ ቢገባውም እንዳላቀረበ ተናግሯል፡፡ ያየሰው አክሎም ከዚህ በፊትም ሥራዬን እንዳልሠራ እያስፈራሩኝ ሥራ አቁሜያለው፤ በሕዝብ ላይ አሳመጸ ከተባለም የደረሰው ጉዳት ሊቀርብ ይገባ ነበር፣ ነገር ግን አልቀረበም ሲል ተደምጧል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት ሐሰተኛ መረጃ አሠራጭተሀል ብለው 5 ጊዜ አስረውኛል ያለው ጋዜጠኛው፣ ለ54 ቀን አዋሽ ታስሮ ቢወጣም ‹‹ጥፋተኛ ተብዬ አልተፈረደብኝም›› ሲል ከዚህ በፊት መታሰሩን ጠቅሷል፡፡

ጋዜጠኛ ያየሰው በየጊዜው በሚደርስብኝ እንግልትና ሰቆቃ ከዕድሜዬ ላይ እየተቀነሰብኝ ነው፤ በተዝረከረከ አሰራር በዘፈቀደ መታሰሬ አግባብነት የለውም ሲል ለፍርድ ቤት አቤቱታ አሰምቷል፡፡ ያየሰው በተደጋጋሚ መታሰሬን የገለጽኩት ጉልበተኛ መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ እኔ በፍርድ ቤት አልተፈረደብኝም በየጊዜው እያሰሩ የችሎቱንም ጊዜ መሻማት የለባቸውም ሲል መታሰሩ አግባብ እንዳልሆነ ተከራክሯል።

ጉዳዩን የተከታተለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ውስጥ 10 ቀን በመፍቀድ የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ለግንቦት 29፣ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል መባሉን ከችሎት ጉዳዮች ዘጋቢዋ ታሪክ አዱኛ ተመልክተናል።።

ፖሊስ በትላንትናው እለት በተመሳሳይ የሳምታዊው ፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ከሥራ ቦታው በቁጥጥር ስር ቢያውለውም፣ እስካሁን ፍርድ ቤት ስለመቅረቡ የታወቀ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img