Saturday, May 18, 2024
spot_img

አቶ ጃዋር መሐመድ አገሪቱ ለገባችበት ችግር ገዥው ፓርቲ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠያቂ አደረጉ

  • ፖለቲከኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሊያገኙኝ ከፈለጉ ዝግጁ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል

አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ ግንቦት 19 2014 በሰኔ ወር 2012 የድምጻዊ ሃጫሉ ሑንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተነሳው ሁከት ጋር በተገናኘ ከሌሎች ታዋቂ ፖለቲከኞች ጋር ታስረው በተያዘው ዓመት ታኅሣሥ መጨረሻ ላይ የተለቀቁት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጃዋር መሐመድ፤ አሁን ኢትዮጵያ ለገባችበት ችግር ገዥው ብልጽግና ፓርቲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በዋነኝነት ተጠያቂ ያደረጉት ከእስር መልስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው፡፡

ከእስር መለቀቅ መልስ የነበሩትን አምስት ወራት በአደባባይ ወጥተው ከመናገር ተቆጥበው የቆዩት ፖለቲከኛው፣ ‹‹ኡቡንቱ›› ከተሰኘ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛ ጋር ባደረጉት ወደ ሁለት ሰአት በተጠጋ ቃለ ምልልስ፤ ስለ እስር ቆይታቸው፣ ከገዥው ፓርቲ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እየሠሩ ነው ስለመባሉ፣ ስለ ሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ስለ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ወቅታዊ ፖለቲካ እና ሌሎችም ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

በቆይታቸው ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከገዥው ፓርቲ ጋር እየሠሩ መሆኑን እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተዋል በሚል አሉባልታ ይናፈሳል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ አሉባልታዎቹን እርሳቸውም በግል እንደሚሰሟቸው ጠቁመው፣ በግል ከማንም ጋር ቁርሾ እንደሌላቸውና ‹‹የታሰርኩትም ቢሆን በፖለቲካ ልዩነት እንጂ በግል ፀብ አይደለም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ አያይዘውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዳልተገናኙ በመግለጽ፤ ‹‹[ዐቢይ] ሊያገኘኝ ከፈለገ ግን ሁሌም ዝግጁ ነኝ›› በማለት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡   

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበሩ፤ ‹‹ሀገራችንን ከጦርነት አስወጥቶ ወደ ሰላም እና ልማት ለመመለስ እድሉ ከተገኘ›› ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ጋር ጦርነት እየገጠመ ካለው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከሚለው ቡድን መሪ ኩምሳ ድሪባ (በሌላ አጠራሩ ጃል መሮ) እና ከሌላኛው ከመንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ ከሚገኘው ሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ‹‹በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ›› ተገናኝቶ ‹ለመሥራት እና ለመተባበር› ቁርጠኛ ነኝ ሲሉም አክለዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹እኔ የማልፈቅደው ከማናቸውም ጋር አብሬ ጦርነት ማፋፋም [ነው]›› ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ሁሉም በጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉም ይሁኑ በጦርነት ውስጥ ያልተሳተፉ ምሁራን እና ሊሂቃን ወደ ሰላም ጠረጴዛ መምጣት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው፤ አገሪቱ አሁን ለገባችበት ችግር ትልቁን ድርሻ የሚወስደውም ሀገር እያስተዳደረ የሚገኘው ገዥው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም እንደመሪ ደግሞ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ›› መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ አግባብ ወደ መፍትሔ የሚገባ ከሆነ የእነሱ ተሳትፎ እና ፍቃደኝነት ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አቶ ጃዋር በቃለ ምልልሳቸው በትግራይ 19 ወራት ስላስቆጠረውና እርሳቸው የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ስላላገኘ ነው እንጂ ከሰሜኑም ይቀድማል ስላሉት በኦሮሚያ እየተካሄደው ስላለው መንግሥት ‹‹የሕግ ማስከበር›› በሚል ስለሚጠራው ጦርነት አንስተዋል፡፡ የጦርነቱን መንስኤ በተመለከተም በሁለቱም አካባቢዎች በ2010 የመጣውን ለውጥ ሽግግር በአግባቡ ማካሄድ ያለመቻል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ለገባበት ጦርነት ለዓመታት በገዥነት የቆየውን የሕወሓት ፓርቲ በድጋሚ ማቀፍ ያለመቻል ያመጣው ነው ያሉት ፖለቲከኛው፣ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለውን ቡድን በተመለከተም የተገባው ቀውስ ከለውጡ በፊት ኢሕአዴግን በጦር የገጠሙ ታጣቂዎችን በለውጡ ማቀፍ ያለመቻል ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

በሌላ በኩል አቶ ጃዋር ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮችን በተመለከተም የተፈጠረው ቀውስ ባለፉት ዓመታት በአማራ ፖለቲካ ውስጥ ብሔርተኝነቱ አያየለ መምጣቱን መታዘባቸውን ‹የቀድሞ ሕይወቴ› ባሉት ከእስር በፊት በነበረው ጊዜ አስተያየት እንደሰጡበት አስታውሰው፤ የተፈጠሩት ነገሮች በክልሉ የተጋጋለውን ብሔርተኝት በወጉ መቆጣጠር ያለመቻል ያመጣው መሆኑን አመልክተዋል፡፡  

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ባለፉት ሁለት ዓመታት ‹‹ለውጡ ከሐዲዱ ወጥቷል›› ያሉት አቶ ጃዋር፣ ይህ መሆኑ የትግራይን ጦርነት ማቀጣጠሉንና ይህን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት የአማራ ክልል ኃይሎችን በአጋዥነት መፈለጉን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ በክልሉ ዳብሯል ያሉት ‹‹ጦረኝነት›› ችግር ሆኖ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ይህን መረዳት እንደነበረበት አስታውሰው፣ ጦርነቱ ጋብ ብሎ ከሕወሓት ጋር ወደ ሰላም ፖለቲካ ሲገባ ይህን ለመቆጣጥር ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢያስፈልግም ውይይት ሲጀመር ቀድሞ በጦርነቱ የተጋበዘውን የአማራ ልሂቅና ወጣት ባለመካተቱ ‹‹ተከድቻለሁ›› የሚል ስሜት ውስጥ እንዲገባ መሠረት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ ከመንግሥት ውጭ ታጣቂ መኖር ባይኖበትም፤ ቀድሞ የተዋጋውን አካል ከድርድሩ አግልሎ ድንገተኛ ውሳኔ አደጋ አለው ያሉት ጃዋር፤ ከዚህ ለመውጣት አቃፊነት እንደሚያስፈግ ጠቅሰዋል፡፡ ፖለቲከኛው ከዚህ ጋር በተገናኘ ‹‹ብዙዎች ላይስማሙበት ቢችሉም›› በማለት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከአማራ፣ ኦሮሞ እና ትግሬ አንዱን ያገለለ ሂደት እንደማይሳካ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ከትግራይ ጋር ሰላም ለመፍጠር ሌላኛውን የአገሪቱን ክፍል ማግለል አያስፈልግም ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ጉዳይ ከወታደራዊ ይልቅ በፖለቲካዊ ምላሽ መፍትሄ ሊገኝለት የሚችል ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ዘለግ ባለው የአቶ ጃዋር ቃለ ምልልስ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ስለቆዩበት የእስር ጊዜያቸውም ተነስቷል፡፡ ፖለቲከኛው ከእስር ቤት ባልጀሮቻቸው ጋር መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ነው ባሉት ምክንያት ባደረጉት የረሐብ አድማ ሰውነታቸው ከስቶ የመታየቱ ምስጢር 30 ያክል ኪሎ ግራም መቀነሳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ የእስር ቤት ቆይታቸው የግል የሕይወት ታሪካቸውን ጽፈው ማዘጋጀታቸውን የገለጹት ጃዋር፤ ወደ ማተሚያ ቤት የመላክ ሒደቱ እንደተቃረበ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጃዋር መሐመድ ትላንት ምሽት ከተላለፈው የኡቡንቱ የአማርኛ ቋንቋ ቃለ ምልልስ በተጨማሪ አንድ ሰዐት ዘግይቶ ቀድሞ ይመሩት በነበረው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ በአፋን ኦሮሞ ሌላ ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img