Saturday, May 4, 2024
spot_img

የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የከተማዋ ሕንጻዎች ግራጫ ቀለም ሊቀቡ ነው የመባሉ መረጃ ሐሰተኛ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 13 2014 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ተዘበራርቋል ያለው የሕንጻዎች ቀለም ወጥ እንዲሆን አደረግኩት ባለው ጥናት ሁሉም ሕንጻዎች ቀለማቸው ግራጫ (ግሬይ) እንዲሆን መወሰኑን ማስታወቁ መነገሩ አይዘነጋም፡፡

ይኸው ለከተማዋ ተመርጧል የተባለው የግራጫ ቀለም ባለፉት ቀናት በተለይ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

በወቅቱ መረጃውን ይዞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ በከተማው የሚገኙ ሕንጻዎች ቀለማቸው ወጥ እንዲሆን ለአንድ ወር ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ከከተማዋ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሥጦታው አካለ እንደነገሩት ዘግቦ ነበር፡፡  ኃላፊው የከተማዋ ሕንጻዎች ተቆጥረው ቀለማቸው የተለየበት ጥናት አብዛኞቹ ሕንጻዎች ግራጫ ቀለም ያላቸው መሆኑን አመላክቷል እንዳሉም ሠፍሯል፡፡ 

ነገር ግን መንግስታዊው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዛሬው እለት ይዞት በወጣው መረጃ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ የከተማዋ ሕንጻዎች ግራጫ ቀለም ሊቀቡ ነው የመባሉ መረጃ ሐሰተኛ ነው እንዳሉት አስነብቧል፡፡

ኃላፊው አክለውም እስካሁን ድረስ የከተማዋ ሕንጻዎች ቀለም ምን ዐይነት ይሁን የሚለው ጉዳይ ለውይይት ቀረበ እንጂ የከተማ አስተዳደሩ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳላሳለፈ መናገራቸው ተመላክቷል፡፡

በቅርቡ በጉዳዩ ላይ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ ይህን መነሻ አድርገው አንዳንድ ግለሰቦች ለግራጫ ቀለም የመሰላቸውን ትርጓሜ ሲሰጡ ተመልክተናል ብለዋል፡፡ ጉዳዩ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደሚዘዋወረው ተግባር ላይ የዋለ ሳይሆን ገና ለምክክር የቀረበ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ከተማዋ ላይ አንድ ዐይነት ቀለም ብቻ ለቀለም ቅብ ሥራ ያስፈልጋል የሚል እሳቤ መያዝ እንደሌለበት የተናገሩም ሲሆን፣ ለአስፈላጊው ሕንጻና አካባቢ የሚመጥን ዝብርቅርቅ ያልሆነና ለዓይን የሚማርኩ ቀለማትን የያዘ ስታንዳርድ እንደሚኖረን ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።

ከሳምንታት በፊት በተደረገው የከተማ አስተዳደሩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ለከተማዋ ሕንፃዎች የቀለም ስታንዳርድ ተግባራዊ የማድረግን ሐሳብ አንስተው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለከተማ ካቢኔ አባላት መመርያ ካስተላለፉባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ስለሆነው የሕንጻዎች ቀለም ጉዳይ ሲናገሩ፣ የከተማዋ ሕንፃዎች ቀለም ወጥነት የሚጎድለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዐቢይ፤ ‹‹እያንዳንዱ ሕንጻ በተፈቀደለት የቀለም ዓይነት ነው እንጂ የሚቀባው፣ የእኔ ስለሆነ ቀለም ስላማረኝ ብሎ ሁላችንም የምናየውን ቀለም እንደፈለገ መቀባት አይችልም፤›› ካሉ በኋላ፣ የካቢኔ አባላት ሊመለከቱት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img