አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 9፣ 2014 ― አሜሪካ በፕሬዝዳንትዋ ጆ ባይደን በኩል የአገሪቱ ወታደሮች ዳግም በሶማሊያ እንዲሰማሩ በትላንትናው እለት ትዕዛዝ ሰጥታለች፡፡
አገሪቱ ከዚህ ቀደም ወታደሮቿን በሶማሊያ ያሠማራችው የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ሠራዊትን በማደራጀት፣ በማሠልጠን እና ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ለማማከር በሚል ነበር፡፡
ነገር ግን ከባይደን በፊት የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ ቀደም ሲል ተሰማርተው የነበሩ የአሜሪካ ወታደሮችን ከአገሪቱ ጠቅልለው እንዲወጡ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሶማሊያ እሑድ እለት አዲስ ፕሬዝዳንት መምረጧን ተከትሎ የአገራቸው ወታደሮች እንደገና በሶማሊያ እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጥተው የነበረ ሲሆን፣ ይህንኑ ትዕዛዝ 10ኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ በደስታ እንደሚቀበሉት መግለጻቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡
አሜሪካ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገዛዝ ዘመን ከሶማሊያ ያስወጣቻቸው ወታደሮች ብዛት 700 ያህል ነው፡፡ አሜሪካ ወታደሮችን ከሶማሊያ ብታስወጣም፣ ፔንታጎን ግን እዋጋዋለሁ በምትለው አልሸባብ ዒላማዎች ላይ የድሮን ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።
አሁን በባይደን ትእዛዝ የተሰጠበትና በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ተቀባይነት ባገኘው እቅድ መሠረት አሜሪካ ወደ ሶማሊያ የምታሠማራቸው ወታደሮች ብዛት ከ500 እንደሚበልጥ ተነግሯል፡፡