Saturday, May 18, 2024
spot_img

የአ/አ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባልተገኙበት ከሲኖዶስ ጋር ውይይት ተካሄደ

አምባ ዲጂታልዐርብ የካቲት 4 2014 ― የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባልተገኙበት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡

የከተማ አስተደዳሩ ባወጣው መረጃ በምክትል ከንቲባው የተመራ የአመራሮች ቡድን በመንበረ ፓትሪያርኩ ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ ‹‹ከብፁአን የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ጋር በቀጣይ ወይይት ስለሚደርግበት ሁኔታ ምክክር›› አድርገዋል፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደሩ ከሆነ ውይይቱ ‹‹በመልካም ሁኔታ ተካሂዷል፡፡››

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ላይ ያልተገኙት በትላንትናው እለት የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በዛሬውም እለት ቀጥሎ በመዋሉ ምክንያት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ባወጣው መረጃ ጥር 25፣ 2014 ከሲኖዶሱ ጋር ተገናኝቶ ውይይት ለማካሄድ ስምምነት ተደርሶ፣ የከተማ አስተዳደሩ ሰዎች በቀጠሮ ቦታ እና በሰአቱ ቢገኙም ሲኖዶሱ ተለዋጭ ቀጠሮ ስለጠየቀ ውይይቱ ሳይሳካ መቅረቱን ገልጾ ነበር፡፡

ኋላም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፈው እሑድ ጥር 29 ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር መገናኘታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በዚሁ ደብዳቤ ከአቡነ ማትያስ ጋር ‹‹ችግሩን በውይይት ፈጥነን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ተወያይተናል›› ብለዋል፡፡ ከንቲባ አዳነች ጥር 30 በጻፉት ደብዳቤ ለየካቲት 2 ሲኖዶሱ ተወካዮቹን ወደ ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዲልክ ጠይቀው ነበር፡፡

በአንጻሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ በበኩሉ የካቲት 1 በጻፈው ደብዳቤ ‹‹ጥር 1፣ 2014 በመስቀል አደባባይ የተከናወነው ሑነት›› የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንን ‹‹እጅግ ያስቆጣ ድርጊት›› መሆኑን በመጥቀስ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ለዛሬ የካቲት 4 በመንበር ፓትርያርኩ እንዲገኙ ሲል ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ደብዳቤ ጽፏል፡፡

የዛሬውን ውይይት ተከትሎ ሁለቱ አካላት ባካሄዱት ውይይት ‹‹ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በጋራ ስምምነት›› ለቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 8፣ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ በመያዝ በቅዱስ ሲኖዶሱ ፅ/ቤት ለመገናኘት በጋራ ተወስኖ ቀጠሮ እንደተያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገልጧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img