አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥር 13፣ 2014 ― በትላንትናው ምሽት በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና በቡራዩ አዋሳኝ ወይ ብላ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ ታቦት በመሸኘት ላይ በነበሩ ምዕመናን እና ፖሊስ መካከል በተከሰተ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነግሯል፡፡
ለሰዎች ሕይወት ማለፍ መንስኤ የሆነው ክስተት መነሻው ምን እንደሆነ ይህ ዘገባ እስተጠናቀረበት ሰዐት ድረስ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የፀጥታ አካላትም ሆነ አጎራባቹ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በይፋ ማብራሪያ አልተሰጡበትም፡፡
ሆኖም የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፣ በተፈጠረው ችግር የሰዎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጦ፣ መንግሥት በስፍራው የተፈጠረውን ክሥተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
አክሎም መንግሥት በዓሉ በተገቢው መንገድ ባለመከበሩ፣ እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ኀዘኑን ገልጧል፡፡
የትላንት ምሽቱን ክስተት በተመለከተ እስካሁን ምከንያቱ ባይገለጽም፣ ታቦት በመሸኘት ሒደት ላይ በነበሩ ምዕመናን ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ሲተኮስ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ተሠራጭቷል፡፡
ምሽቱን የወይብላ ምርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ታቦት ከመንገድ ማለፍ ባለመቻሉ ወደ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስትያን እንዲመለስ መደረጉ ሲገልጽ፣ በዛሬው እለት ደግሞ ወደ መንበረ ክብራቸው መግባቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዛሬው የሽኝት ሥነ ሥርዐት ላይ የአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ መልከ ጼዴቅ ተገኝተው ምዕመናንን ማጽናናታቸውም ተነግሯል፡፡
ምሽት በአዲስ አበባ ከተማ ወይብላ ቅድስት ማርያም እና የቅዱስ ሚካኤል ታቦት ሽኝት ላይ የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ ድርጊቱን ያወገዙ በርካቶች በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ቁጣቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡