አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 30፣ 2014 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከእስር መፈታታቸውን አወድሰው መግለጫ አውጥተዋል።
ዋና ጸሐፊው በመግለጫቸው ሁሉም አካላት አጋጣሚውን ተኩስ ለማቆም፣ ሁሉን ያማከለ አገራዊ ውይይት ለማካሄድ እና ለእርቅ እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።
በትላንትናው እለት ከአንድ ዓመት በላይ እስር ላይ የነበሩት ታዋቂዎቹ ፖለቲከኞች አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ስብሐት ነጋ እና የሕወሓት የቀድሞ አመራሮች ከእስር መለቀቃቸው ይታወቃል።
ከፖለቲከኞቹ በተጨማሪም በጃዋር መሐመድ መዝገብ ተከሳሽ የነበረው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ መሰለ ድሪብሳ ከእስር ተለቋል።
የፖለቲከኞቹን ከእስር መለቀቅ ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ክሳቸው እንዲነሳ የተደረገው በቀጣይ የሚደረገውን ሃገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን አስታውቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ እነ ስብሐት ነጋ የተለቀቁት ደግሞ የጤና እና የዕድሜ ሁኔታን ከግምት በማስገባት ነው ብሏል።
ሐሙስ ታኅሣሥ 28 የገና በዐል መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ መበዳደሎችን ለመሻር በዚህ ሰአት ሀገራዊ እርቀ ሰላም ያስፈልገናል ማለታቸው መነገሩ አይዘነጋም።
በተመሳሳይ በትላንትናው እለት ባወጡት ሌላ መግለጫ፣ ‹‹አሁን የገጠምነው ጦርነት በሰላም እንዲጠናቀቅ እናደርጋለን›› ብለዋል። ይህንኑ መግለጫ ካወጡ ከሰዓታት በኋላ ፖለቲከኞቹ ተፈተዋል።