Friday, November 22, 2024
spot_img

ፌልትማን በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ ያቀናሉ ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 27 2014 ― የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ነገ ሐሙስ ታኅሣሥ 28 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ ተዘግቧል፡፡

ሬውተርስ የዜና ወኪል አንድ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ፌልትማን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመወያየት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ግጭት እንዲያበቃ ግፊት ያደርጋሉ፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን፣ ከተሾሙበት ባለፈው ዓመት መገባደጃ አንስቶ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለሱ ቆይተዋል፡፡

ልዩ መልእክተኛው ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያን የጎበኙት በኅዳር ወር አጋማሽ ገደማ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቆይታቸው የሕወሓት ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ መቃረባቸው የተነገረበት ነበር፡፡ ፌልትማን በዚሁ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሕወሓት መሪዎች ጋር መገናኘታቸውን ገልጸዋል፡፡  

ከኢትዮጵያ ቆይታቸው በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱት ፌልትማን፣ የጦርነቱን መባባስ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ለመምከር ቱርክ እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ ወደ ግብፅ አቅንተው ነበር፡፡

አምባሳደሩ አሁን ወደ ኢትዮጵያ በሚያቀኑበት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተቃርበው የነበሩት የሕወሓት ኃይሎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር ማቅናታቸውን ተከትሎ የፌዴራል መንግስት ባካሄደው ማጥቃት ከአማራና አፋር ክልሎች ወጥተዋል፡፡

ሆኖም የሕወሓት መሪዎች አካባቢዎቹን ለቀን የወጣነው ለሰላም እድል ለመስጠት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በተያዘው ወር አጋማሽ ከቢቢሲ ኒውስ አወር ጋር ቆይታ ያደረጉት ፌልትማን፣ የሕወሓት ኃይሎች ከአፋር እና አማራ ክልሎች መውጣታቸውን ሰላም ለማምጣት ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ነበር፡፡

በቅርብ ቀናት ጋብ ያለው በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ከተጀመረ 14 ወራት ተቆጥረዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img