Tuesday, December 3, 2024
spot_img

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለኦሚክሮን ዝርያ መፈጠር ጠባብ ብሔርተኝነት እና የክትባት ክምችት ተስማሚ ሁኔታ ፈጥሯል አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 23፣ 2014 ― የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ ለሚገኘው አዲሱ የኮሮና ቫረስ ልውጥ ኦሚክሮን መፈጠር ‹‹ጠባብ ብሔርተኝነት እና የክትባት ክምችት›› ተስማሚ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አዲሱን ቫይረስ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፣ አሁን ላይ ኮሮና ቫይረስን ለማከም የተሻሉ መንገዶች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ፍትሐዊ የሆነ የክትባት ክፍፍል ባለመኖሩ ግን ቫይረሱ ቅርጹን እየቀያየረ እንዲከሰት ዕድል ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአንዳንድ አገራት ‹‹ጠባብ ብሔርተኝነት እና የክትባት ክምችት ፍትሐዊነትን አጓድሏል›› ያሉት ዶክተር ቴድሮስ፣ ይህ ለኦሚክሮን ዝርያ መፈጠር ተስማሚ ሁኔታዎችን እንደፈጠረ ነው የገለጹት፡፡

አክለውም ‹‹ቫይረሱ እየተለዋወጠ በመጣ ቁጥር የመቆጣጠር እና የመተንበይ አቅማችን እየቀነሰ ይሄዳል›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ኢ-ፍትሐዊነትን ከገታን ወረርሽኙን እንገታዋለን›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ እና በአሜሪካ ሰዎች ቢያንስ አንድ ዙር የኮሮና ቫይረስ ክትባት የወሰዱ ቢሆንም፣ የዓለም የጤና ድርጅት የአውሮፓዊያኑ 2021 ከመጠናቀቁ በፊት በመላው ዓለም ቢያንስ 40 በመቶ ሕዝብ ክትባት እንዲያገኝ ያቀደው ዕቅድ በተለይም በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ሳይሳካ ቀርቷል።

ዶ/ር ቴድሮስ ከዚህ ቀደም የበለፀጉ አገራት የዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦትን በማግበስበስ አብዛኛው ሕዝባቸውን ሁለት ዙር ሲከትቡ ሌሎች የመጀመሪያውን ዙር ክትባት እየተጠባበቁ ይገኛሉ በማለት ወቅሰዋል።

እስካሁን በመላው ዓለም በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ287 ሚሊዮን የተሻገረ ሲሆን፣ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img