አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 23፣ 2014 ― የቤንሻጉል ሕዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ (ቤሕነን) የቀድሞ ሠራዊት መሪ ዐብዱልዋሐብ መሐድ ታስሮ ከነበረበት አሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት ማምለጡ ተነግሯል።
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አንድ ሥማቸው ያልተገለፀ የክልሉን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የ9 ዓመት ዕሥር የተፈረደበት አብዱልዋሐብ ያመለጠው ታኅሣሥ 18፣ 2014 ነው።
ግለሰቡ ከዚህ በፊትም እንዲሁ 2001 የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም፣ 2002 ላይ ከማረሚያ ቤት አምልጦ ወደ ኤርትራ በመግባት ኢትዮጵያን ከሚወጉ ኃይሎች ጋር ሲሠራ እንደነበር ተገልጿል።
ከዚያ በመቀጠል 2009 ላይ የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥት ግለሰቡ ከሚመራው ቡድን ጋር ባደረጉት የሠላም ድርድር ተስማምቶ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ሠላማዊ ኑሮ መምራት ጀምሮ ነበር።
ግለሰቡ ይመራቸው የነበሩ ታጣቂዎች ከመንግሥት 20 ሚሊዮን ብር መቋቋሚያ ተቀብለው ተበታትነው ከቆዩ በኋላ፣ ሰኔ 2010 ዳግም አሶሳ ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት መሪው ራሱ ተሳታፊ በመሆን የሰው ነፍስ ማጥፋቱም ነው የተገለጸው። በዚህም ግለሰቡ ተከሶ ሲከራከር ከቆዬ በኋላ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ16 ዓመት ከስድስት ወር ዕሥራት ተፈርዶበት እንደነበር ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ፍርደኛው ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ አቅርቦ ቅጣቱ ወደ ዘጠኝ ዓመት ዕሥር ዝቅ ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም፣ ዐቃቤ ሕግ በቅጣት ውሳኔው ባለመስማማቱ በፍርድ ክርክር ሒደት ላይ ሳለ ግለሰቡ አምልጦ መጥፋቱ ነው የተነገረው።
ግለሰቡ ፍርድ የተሠጠው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ሆኖ ለቤተሰብ እንዲቀርብ በሚል ወደ አዲስ አበባ ሌሎች ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች እንዳልተወሠደ ነው የተጠቆመው።
ታሳሪው በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት በጥብቅ ሲፈለግ እና ከፍተኛ ክትትል ሲደረግብት የነበረ ከመሆኑም አንጻር፣ በርካታ ዕሥረኞች ካሉበት ማረሚያ ቤት ቀን ላይ በግልጽ ለሁለተኛ ጊዜ ማምለጡ፣ ሴራ ሳይኖርበት እንዳልቀረ ያመላክታል ሲሉ ስማቸው ያልተገለፀው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊው መጠቆማቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።
በአሁን ሰዓት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፀጥታ ኃይሎች እሥረኛውን እየፈለጉት ቢሆንም ቦታው ለሱዳን ካለው ቅርበት እንዲሁም ሰውዬው መውጫ እና መግቢያውን የሚያውቅ፣ በትግልም ለ20 ዓመት ገደማ የቆዬበት በመሆኑ በቀላሉ ሊገኝ ይችላል ተብሎ እንደማይታሰብ ነው የሥራ ኃላፊው የገለጹት።
ግለሰቡ ሱዳን ከገባ በኋላም እንደከዚህ ቀደሙ ወጣቶችን መልምሎ በማሠልጠን፣ በመተከልና አሶሳ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ የሆነ የሽብር ድርጊቱን ሊቀጥል እንደሚችል ነው የተመላከተው።