አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 19፣ 2014 ― የሶማሊያ ግንድ ያላቸው የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ኢልሃን ዑመር የሥልጣን ጊዜያቸው ካበቃ አንድ ዓመት አልፎቸዋል ያሏቸው የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዐብዱላሂ መሐመድ ፋርማጆን ከቦታቸው ዘወር እንዲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢልሃን በትዊተር ባሰፈሩት ማስታወሻ ፋርማጆ ከቦታቸው ዘወር ብለው የዘገየው የሶማሊያ ምርጫ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የኢልሃን ከቦታዎ ዘወር ይበሉ የሚል ጥሪ የመጣው ፋርማጆ የአገራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሑሴን ሮብልን ከሥልጣናቸው ካገዱ በኋላ ነው፡፡
ፋርማጆ ሮብልን ያገዱት ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ መሆኑን የአገሪቱ ብዙኃን መገናኛዎች ይዘዋቸው የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ሁለቱ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት በኮሮና ምክንያት ከተረዘመው የአገሪቱ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ሲገቡ የቆዩ ናቸው፡፡
እግዱን ተከትሎ የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ሞሐመድ ኢብራሂም ሞአሊሙ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ ተቃውመውታል።
ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሁድ ዕለት የምክር ቤት ምርጫን በማደናቀፍ አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲከሱ ተሰምተው ነበር።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የሶማሊያ ባሕር ኃይል አዛዥ የሆኑትን ጄነራል አብዲሃሚድ ሞሐመድ ዲሪርንም ከኃላፊነታቸው አግደዋል።