አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 18፣ 2014 ― የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ ዐብዱላሒ መሐመድ (ፋርማጆ) የአገራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሑሴን ሮብልን ከሥልጣናቸው አግደዋል፡፡
ፋርማጆ ሮብልን ያገዱት ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ መሆኑን የአገሪቱ ብዙኃን መገናኛዎች ይዘዋቸው የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ሁለቱ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት በኮሮና ምክንያት ከተረዘመው የአገሪቱ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ሲገቡ የቆዩ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት መሐመድ ፋርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀል ምርመራ ላይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ከሥልጣናቸው ቢያግዱም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሁሴን ሮብሌ ግን ፕሬዜዳንት መሐመድ ፋርማጆ ሕገ መንግስቱን በመጣስ ቢሮዬን በወታደራዊ ሃይል ለመቆጣጠር ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ለሚፈጠረው መዘዝ ሁሉ ኃላፊነቱን የሚወስዱት ፋርማጆ ናቸው እያሉ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሑሴን ሮብል ባሳለፍነው እሁድ ፕሬዘዳንቱ የሶማሊያ ምርጫን ለማጭበርበር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ ነው በሚል ተችተዋል፡፡
መሐመድ ሁሴን ሮብሌ
የፕሬዝዳንቱን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውዝግብ ተከትሎ አሜሪካ በሶማሊያ በሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲን በኩል መሪዎቹ ውጥረቱን ለማርገብ ከግጭት ቀስቃሽ ድርጊቶች እንዲታቀቡ እና ሁከትን ለማስወገድ ርምጃዎችን እንዲወስዱ አጥብቃ አሳስባለች።