አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 13፣ 2014 ― የኦሮሞ ፌዴራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባለፈው ኅዳር ወር አጋማሽ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳዮች በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ለ18 ወራት የሚቆይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ጥሪ ማቅረቡ ከምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ገብሩ ገብረማርያም ተቃውሞ አስከትሎበታል፡፡
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔውን ሲያሳልፍ ተሳታፊ እንዳልነበሩ ለጀርመን ድምጽ የተናገሩት አቶ ገብሩ፣ ፓርቲያቸው በዚህ ወቅት ያወጣውን መግለጫ ‹‹ዐይን ያወጣ አገር የማፍረስ ተግባር ነው›› ብለውታል፡፡
በሌላ በኩል በስብሰባው ላይ የተሳተፉትና ውሳኔውን ካሳለፉት መካከል የሆኑት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፣ አቶ ገብሩ በስብሰባው ላይ በአካል እንዲገኙ ቢነገራቸውነም ሊገኙ አልቻሉም ብለዋል፡፡ አያይዘውም አቶ ገብሩ ባልተገኙበት ስብሰባ ላይ የተወሰነውን ውሳኔ በግል ሚዲያ ወጥተው ተቃሞ ማንጸባረቃቸውን የተቹ ሲሆን፣ አጀንዳ አሲይዘው መወያየት ይችሉ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ ተቃውሞ የሰነዘሩት አቶ ገብሩ ገብረማሪያም የኦፌኮ አባል ሆነው ይቀጥላሉ ወይስ አይቀጥሉም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ እያሰብኩበት ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው አቶ ገብሩ ራሳቸውን ማግለል ከፈለጉ መብታቸው ብለዋል፡፡
በአመራሮቹ መካከል ልዩነት የተፈጠረበት ኦፌኮ፣ ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአሁኑ ጊዜ በአገር ውስጥ የማይገኙ ሲሆን፣ አመራር አባሎቹ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ በእስር ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡