አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 8፣ 2014 ― የቀድሞ ፕሬዝዳንትዋ ጃኮብ ዙማ ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ በወሰነችው ደቡብ አፍሪካ፤ በጸጥታ ስጋት ሰበብ ፖሊስ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከዚህ በፊት በሕክምና ሰበብ የተለቀቁበት ምክንያት ሕገ ወጥ ነው በማለት ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ የወሰነው ከትላንት በስትያ ታኅሣሥ 6፣ 2014 ነበር፡፡
በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በሙስና ላይ በተካሄደው ምርመራ ላይ ለመቅረብ አሻፈረኝ በማለታቸው የታሠሩት ጃኮብ ዙማ፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ ባልተገለጸ የጤና ችግር ከእስር ቤት መውጣታቸው አይዘነጋም፡፡
የ79 ዓመት እድሜ ያላቸው አዛውንቱ ዙማ፣ በሐምሌ ወር በተነሳ ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ራሳቸውን ለፖሊስ አስረክበው እስራቸውን ጀምረው የነበረ ቢሆንም፣ እስራቸው በአገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ የሰዎችን ሞት እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከትሏል፡፡
በዚሁ ተቃውሞ ዙማ ጠንካራ ድጋፍ እንዳላቸው በሚነገርላት በኩዋዙሉናታል ግዛት ከ300 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡