Sunday, October 6, 2024
spot_img

ከታሠረ አራት ቀናት ያስቆጠረው ታምራት ነገራ፤ አሁንም ያለበት ሥፍራ አልታወቀም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 4፣ 2014 ― ባለፈው ዐርብ ከመኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው ታምራት ነገራ፣ አሁንም ድረስ የታሠረበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ቤተሰቦቹ ገልፀዋል።

እንደ ቤተሰቦቹ ከሆነ ታምራት የት እንደታሰረ ባለመታወቁ ምግብ ልብስና መድሃኒት ሊያደርሱለት አልቻሉም።

የሚሠራበት ተራራ ኔትወርክ እንዳስታወቀው ቤተሰቦቹ ቀድሞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢያቀኑም፣ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ተዛውሯል ተብለው ወደ ስድስት ኪሎ የሄዱ ቢሆንም፣ ወደዚያ እንዳልተዘዋወረ ተነግሯቸው ተመልሰዋል።

ቅዳሜ ዕለት በተመሳሳይ ቤተሰቦቹ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ መምሪያ ያቀኑት ቤተሰቦቹ፣ ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ፖሊስ በመሆኑ ግሎባል አካባቢ በሚገኘው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሄዳችሁ አጣሩ ተብለው እዚያም እንዳልመጣ ተነግሯቸዋል።

ይልቅኑም ወደ ቡራዩና ገላን ከተሞች ሄዳችሁ አጣሩ የተባሉት የታምራት ቤተሰቦች፣ በቡራዩ ከተማ በሚገኙ ሶስት ፖሊስ ጣቢያዎች በተጨማሪም ገላን ከተማ ወደ ሚገኘው ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቢያቀኑም ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የተገለፀው።

ከዚህ በተጨማሪም ሜክሲኮ የሚገኘውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቢያናግሩም ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ክልል በመሆኑ እኛጋ አልመጣም የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ታምራት ነገራ ዐርብ ጧት በፖሊስ ከመኖሪያ ቤቱ ሲወሰድ፣ የጸጥታ አካላት የመኖሪያ ቤቱ እና ቢሮውን በመፈተሽ ለመረጃ ይፈለጋሉ ያሏቸውን የሚዲያ ዕቃዎች በሙሉ መውሰዳቸው ቢነገርም ለምን እንደታሰረ የተገለጸ ነገር የለም።

ከሰሞኑ ከታምራት ነገራ በተጨማሪ በኡቡንቱ ሚዲያ የሚሠራው አክቲቪስት እና የፖለቲካ አስተያየት ሰጪው እያስጴድ ተስፋዬ መታሠሩ መነገሩ አይዘነጋም።

ቅዳሜ እለት ደግሞ ሮሃ ቲቪ የተባለ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛ መስራቿ እና በፕሮግራም አቅራቢነት የምትሠራው መዐዛ መሐመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏ ተሰምቷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img