አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 2፣ 2014 ― በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሐሮ ሊሙ ወረዳ፣ 19 ንጹኃን ሰዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ኦነግ ሸኔ መገደላቸው ተሰምቷል።
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ እንደዘገበው፣ ኅዳር 24፣ 2014 መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚለው ቡድን ታጣቂዎች በሠነዘሩት ጥቃት 10 ንጹኃን ዜጎች ሲገደሉ፣ 20 የቀን ሠራተኞች ታግተዋል።
አስሩ ሰዎች ከመገደላቸው በፊት፣ ዘጠኝ ንጹኃን ዜጎች እንደተገደሉና 12 ሰዎች እንደታገቱ የተመላከተ ሲሆን፣ በሳለፍነው ሳምንት በአጠቃላይ 19 ንጹኃን ዜጎች መገደላቸውንና 32 ሰዎች መታገታቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ሰዎቹ የተገደሉት በሊሙ ወረዳ መንደር ስደስት እና መንደር ሰባት ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ነው ተብሏል።
ይህንኑ ተከትሎ የአካባቢው ማኅበረሰብ ቤቱን ለቆ እየወጣ፣ አዝመራው እየተዘረፈ ከመሆኑም ባሻገር፣ በታጣቂ ቡድኑ እጅ ውስጥ ያሉ የመንደር አንድ፣ ስድስት፣ ሰባት፣ ስምንትና ዘጠኝ በርካታ ነዋሪዎች በችግር ላይ ናቸው ተብሏል።
ጋዜጣው ኦነግ ሸኔ የአካባቢውን ነዋሪዎች ካገተ በኋላ ከመግደሉ በፊት “ብር አምጡና ትለቀቃላችሁ” በማለት ብር እንደሚቀበል የተጠቆመ ሲሆን፣ የሚፈልገውን ብር ከተቀበለ በኋላም መግደሉን እንደማይተው ነው ያስረዱት።
በጉዳዩ ላይ የአካባቢው ባለስልጣናት የተናገሩት ስለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም።