Thursday, November 21, 2024
spot_img

የደሴና ኮምቦልቻ መጋዘኖቹ በሕወሓት የተዘረፉበት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአካባቢዎቹ እርዳታ አቋርጫለሁ አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 30፣ 2014 ― በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር የሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአማራ ክልል ከተሞች በሆኑት ደሴና ኮምቦልቻ የነበሩት መጋዘኖቹ በሕወሓት ኃይሎች በመዘረፋቸው በአካባቢዎቹ የምግብ እርዳታ አቋርጫለሁ ብሏል፡፡

ሬውተርስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱያሪክን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የሕወሓት ኃይሎች በዓለም ምግብ ፕሮግራም የነበሩ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህጻናት የሚቀርቡ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ አቅርቦት ክምችት ወስደዋል፡፡

የሕወሓት ታጣቂዎች የእርዳታ ምግብ ተከማችተውባቸው የነበሩት መጋዘኖቹን በዘረፉበት ወቅት በስፍራው በነበሩ ሠራተኞቹ መሳሪያ ተደግኖባቸው ስለነበር መከላከል ሳይችሉ ቀርተዋል ነው የተባለው፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥታቱ ድርጅት የመንግሥት ወታደሮች ሦስት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎችን ለራሳቸው አገልግሎት ተጠቅመዋል ሲል ክስ አቅርቧል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘኖች የተዘረፉባቸው የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች እስከ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ በሕወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የነበሩ ሲሆን፣ ከሰኞ ኅዳር 27፣ 2014 ወደ መንግስት ቁጥጥር ተመልሰዋል፡፡

መጋዘኖቹ የተዘረፉበት ዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን ከአንድ ሳምንት በፊት አሳውቆ ነበር፡፡

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወስጥ የሚገኙ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ ሕይወት እየገፉ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ማለትም 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ አዳጋች የሆኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ናቸው ብሎ ነበር።

ድርጅቱ ከቀናት በፊት እንዳስታወቀው ደግሞ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ለሚያቀርበው ድጋፍ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት አጋጥሞታል፡፡

አጋጥሞኛል ያለው የገንዘብ እጥረት በሰሜን ኢትዮጵያ ለ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በአስቸኳይ ለሚያቀርባቸው የምግብና የአልሚ ምግቦች የሚውለውን 316 ሚሊዮን ዶላር ይጨምራል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img