አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 27፣ 2014 ― ከተለያዩ አገራት አልባሳትና ጫማን ጨምሮ ወደ ሀገር ይዘው የሚገቡ ተመላላሽ ነጋዴዎች ምንም ዐይነት እቃ ይዘው እንዳይገቡ ተከላክሏል፡፡
የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ የገቢ ዕቃዎች ክልከላና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የክልከላው ምክንያት ለንግድ የማይውሉ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ዝርዝር ለመወሰን የወጣውን መመሪያ 51/2010ን በመጠቀም በተመላላሽ መንገደኞች ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ነገር ግን ለንግድ አላማ እየዋሉ የሚገኙ ዕቃዎች በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና በመፍጠራቸው መሆኑን ገልጧል፡፡
ኢትዮጵያ ቼክ ድረ ገጽ በጽሕፈት ቤቱ የደንበኞች ትምህርት ቡድን አባል የሆኑት አቶ ምትኩ አበባው ‹‹አንድ መንገደኛ ሁሌ የሚመላለስ ከሆነ ያለቀረጥ ሁሌም እየተመላለሰ የሚያመጣ ከሆነ በህጋዊ መልኩ በኮንቴነር የሚያስጭኑና ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎችን ኪሳራ ዉስጥ የሚያስገባና ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ይህ ደብዳቤ ወጥቷል›› እንዳሉት አስፍሯል፡፡
የግል መገልገያ ዕቃዎች መመሪያ ቁጥር 51/2010 ስራ ላይ መዋሉን ተከትሎ በተለይ አልባሳትና ጫማዎች በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት መጀመራቸውና ከህጋዊ ነጋዴዎችም አቤቱታና ተቃውሞ ሲቀርብ መቆየቱንም አቶ ምትኩ አበባው መናገራቸው ተመላክቷል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም መንገደኛ ከቀረጥ ነጻ ይዞ እንዲገባ የተፈቀዱ አልባሳትና ጫማዎችን ጨምሮ ዕቃዎችን ተገቢውን ቀረጥና ታክስ መክፈል እንደተጠበቀ ሆኖ ለንግድ እላማ የሚውል ነው ተብሎ ከታመነ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅጣት ይስተናገዳል ያሉት አቶ ምትኩ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ይዞ የሚመጣ ከሆነ ግን በወንጀል መጠየቅ ድረስ የሚያስደርስ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
በአንጻሩ ጠቅልለው ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱ መንገደኞችን በተመለከተ ደግሞ ጓዞቻቸውን ይዘው ቢመጡም ሆነ በካርጎ ቢልኩ በመመሪያ 51/2010 የተፈቀደና ሲገለገሉበት የቆየ ዕቃ ከሆነ ከቀረጥ ነጻ ማስገባት ይችላሉ ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በመመሪያዉ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የተፈቀዱ ቢሆኑም ዕቃዎቹ አዳዲስ እስከሆኑ ድረስ ቀረጥና ታክስ እንደሚከፈልባቸው ተነግሯል።