አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 18፣ 2014 ― ባለፈው እሑድ ዳግም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው የተመለሱት ዐብደላ ሐምዶክ የሱዳን ጦር ከአንድ ወር በፊት የወሰደውን እርምጃ ቀድመው ያውቁ እንደነበር የተናገሩት የሱዳን ሉዓላዊ ም/ ቤት ምክትል ኃላፊ ጀኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሄሜቲ ናቸው፡፡
ሄሜቲ ከአልጀዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሐምዶክ የሱዳን ጦር የወሰደውን እርምጃ ቀድመው እንደሚያውቁት ከመግለጻቸው በተጨማሪ፣ የወራት የንግግር ውጤት እንደሆነ እና ሙሉ በሙሉ ተስማምተው የተደረገ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
በአገሪቱ የሱዳን ጦር አዛዥ ዐብዱልፈታህ አልቡርሃን በመሩት የመፈንቅለ መንቅለ መንግስት እርምጃ ጦሩ የሲቪል አስተዳደሩን ባስቀገድ ዐብደላ ሐምዶክን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናትን ወደ እርስ ቤት ልኮ ነበር፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ መጀመሪያ በጦሩ መሪ አልቡርሃን ቤት በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ተነግሮ የነበረ ሲሆን፣ ኋላም ወደ ቤታቸው ተመልሰው በቁም እስር ቆይተዋል፡፡
ከእርምጃው በፊት ስለነበረው ሁኔታ ያስረዱት ሄሜቲ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በስብሰባዎች ላይ ሁለት ሃሳቦችን ማቅረባቸውን ጠቅሰው፣ ሦስት ምርጫዎች ቀርተዋቸው እንደነበርና፣ ከአማራጮቹ መካከል ጥሩ ነው ያሉት አሁን የወሰዱት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሄሜቲ ይህ እርምጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ስምምነት የነበረውመሆኑን በመጥቀስ፣ ‹‹እኛ በራሳችን እንዲህ አይነት እርምጃ አልወሰድንም›› ሲሉ ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በቁም እስር ላይ የቆዩት ሐምዶክ እሑድ እለት በዋነኛነት በጦር አዛዡ ሌተናል ጀነራል ዐብዱልፈታህ አል ቡርሀን ጋር ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፣ በሁለቱ ባለስልጣናት መካከል የተፈረመው ስምምነት በ14 ጉዳዮችን ዙሪያ ያተኮረ ስለመሆኑ ተነግሮለታል፡፡
መሪዎቹ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና አንድ ወጥ የሆነ የሱዳን ጦር መመስረት፣ የሱዳንን ግዛታዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ የሽግግር ጊዜውን የሚመራውን ሕገ መንግሥታዊ፣ ህጋዊ እና ፖለቲካዊ አሰራሮች መወሰን የሚሉት ይገኙበታል።
ስምምነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላህ ሐምዶክን ወደ ቀደመ ሥልጣናቸው የመለሰ ሲሆን፣ ከስምምነቱ በኋላ ሐምዶክ ባደረጉት ንግግር አንድነት ለሱዳን አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፣ የአገሪቱን ጥቅም ማስጠበቅ ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡