Sunday, September 22, 2024
spot_img

በእነ አቶ እስክንድር ነጋ መዝገብ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 17 2014 ― በእስር ላይ የሚገኙትን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የመዝገቡን ተከሳሾች ጉዳይ የሚመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ችሎቱ በዛሬው ውሎው በትላንትናው እለት መቅረብ የነበረባቸው እነ አቶ እስክንድር ነጋ ተለይተው ለምን እንዳልቀረቡ የማረሚያ ቤት አስተዳዳር ቀርቦ እንዲያስረዳ ባዘዘው መሠረት የታራሚዎች አስተዳደር ዳይሬክተር ኮማንደር አስቻለው መኮንንን ምላሽ ሰምቷል፡፡

ኮማንደሩ በሰጡት ማብራሪያ የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ታራሚዎችን ወደ ዝዋይ ወስዶ እንደ አዲስ በማጀራጀት ሂደት ላይ መሆኑን ተከትሎ ካለው የስራ ጫና አንጻር የተወሰነ ሃይል ወደ ዝዋይ በመሔዱ ምክንያት የሰው ኃይል እጥረት ማጋጠሙን በመጥቀስ፣ ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ታራሚዎች ተለይተው ለራሳቸው ለደህንነት ታሳቢ ተደርጎ እንዲቀሩ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

አክለውም የእስረኞቹን መብት ለማጣበብ እንዳልሆነ የገለጹት ኮማንደር አስቻለው፣ የፍርድ ቤቱን ትዛዝ እንደሚያከብሩ እና ማረሚያ ቤቱ ያለበትን የስራ ጫና እንዲረዳቸው ጠይቀዋል።

ምላሻቸውን የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ የቀረበው ምክንያት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ተቀባይነት ያለው ነው በማለት ማረሚያ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ ተከሳሾችን እንዲያቀርብ በማዘዝ ቀሪ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለታኅሣሥ 11፣ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች ታሳሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በ2012 ሰኔ ወር ላይ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img