አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 16፣ 2014 ― በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ግለሰቦች እንዲፈቱ በማድረግ የተጠረጠሩት የከተማው የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ታዬ ሀብተጊዮርጊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።
የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ያለ ኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ከማቆያ እንዲወጡ አድርገዋል በሚል መሆኑን የከተማው ሰላም እና ደህንነት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል እሸቴን ጠቅሶ ፋና ዘግቧል።
በዚህ ወንጀል የተሳተፉ ሌሎች አመራሮች መኖራቸውን በተመለከተም ከህዝብ ጥቆማዎች እየደረሳቸው እንደሚገኝም አቶ ዳንኤል መግለጻቸውን ዘገባው አክሏል።
በሌላ መረጃ በደብረ ብርሃን ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ከነዋሪዎችና መታወቂያ ካላቸው ሰዎች ውጪ በቀን እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይቻል ተገልጿል።
ክልከላው በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ሰርጎ ገቦችን ለመለየትና አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ነጻ ለማድረግ እንዲያስችል መሆኑን የገለጸው የከተማው አስተዳደር፣ ሰርጎ ገቦች በከተማዋ ገብተው አካባቢን የማጥናትና መረጃ የመስጠት ስራ እየሰሩ እንደሆነ እንደተደረሰበት፣ ይህም ለከተማውና ለነዋሪዎች ደህንነት ሲባል ከከተማዋ ነዋሪዎችና መታወቂያ ካላቸው ሰዎች ውጪ በከተማው በየትኛውም አካባቢ በቀን እንቅስቃሴ ማድረግ የማይቻል መሆኑን አስታውቋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የተጠለሉ ወገኖችም በተዘጋጀላቸው መጠለያ እንዲገቡም አስተዳደሩ አሳስቧል።