አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 15፣ 2014 ― የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የፀረ ሽብርና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ዐብዲ ኢሌን ጨምሮ 13 ተከሳሾች ችሎት የማይቀርቡ ከሆነ መዝገቡን ሊዘጋው እንደሚችል ያስጠነቀቀው በዛሬው ቀጠሮ ባለመገኘታቸው ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ለዛሬ በያዘው ቀጠሮ ምስክር ለመስማት የተሰየመ ቢሆንም፣ የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲሌን ጨምሮ 13 ተከሳሾች ግን ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
ታሳሪቹን የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት የፌደራል ማረሚያ ቤቱ በሀገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ተከሳሾቹ በልዩ እጀባ የሚታጀቡ በመሆናቸው የፌደራል ፖሊስ አጃቢዎች ግንባር ላይ በመሆናቸውና የሰው ኃይል ዕጥረት ስላጋጠመን ማቅረብ ስለማንችል የተራዘመው ቀጠሮ ይሰጠን ሲል በጽሑፍ አመልክቷል፡፡
ሆኖም ለዚህ ማመልከቻ የተከሳሽ ጠበቆች ጥያቄው የተከሳሾቹን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን የሚያጣብብ ነው ሲሉ መቃወሚያ አሰምተዋል። አያይዘውም የቀረበው ምክንያት አሳማኝ አደለም ያሉት ጠበቆቻቸው፣ በባለፈው ቀጠሮ እንዲቀርቡ በፍርድ ቤቱ የተሰጠ ትዛዝ ያላከበረ ነው ተደምጠዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ጦርነት ያለበት የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ስራ ላይ በሆኑበት እና እዚህም ስራ የተሰራ ባለበት ሁኔታ ለምን ታራሚዎችን ማምጣት አልቻላችሁም፣ ያቀረባችሁትም ምክንያት አሳማኝ እና ግልጽ አደለም ሲል ማረሚያ ቤቱ በጽሁፍ ያቀረበውን ማመልከቻ አልተቀበለውም።
በዚህም መሰረት በይደር ተከሳሾቹ እንዲቀርቡ ትዛዝ የሰጠው ፍርድ ቤቱ ታራሚዎች የማይቀርብ አካል ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳሰበ ሲሆን፣ ለተከታታይ ሶስት ቀጠሮ ያለምክንያት ተከሳሾቹን የማያቀርቡ ከሆነ መዝገቡን ዘግቼ አሰናብታቸዋለሁ ሲል አሳስቧል፡፡