Sunday, November 24, 2024
spot_img

ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ሦስት የአካባቢ ባለሥልጣናት ባደፈጡ ታጣቂዎች መገደላቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 14 2014 ― በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳቀኚ ወረዳ ሦስት የአካባቢው ባለሥልጣናት ባደፈጡ ታጣቂዎች ሲገደሉ አንደኛው የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ተፈጽሟል በተባለው ግድያ የሞቱት ባለሥልጣናት፣ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ መሆናቸውን የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጋቢሳ ነግረውኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ግለሰቦቹ ወደ አምቦ ከተማ ሄደው ሲመለሱ በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና የድርጊቱ ፈጻሚዎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡

ግድያው የተፈጸመባቸው የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ኃላፊው አቶ ለሚ ገብሬ፣ የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ተጠሪ ወ/ሮ ደራርቱ ተስፋዬ እና የወረዳው የኅብረት ሥራ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዱጋሳ መሆናቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን ኮምዩኒኬሽን አቶ ተስፋዬ ምሬሳ ገልጸዋል።

በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አብደና አብሹ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው መትረፋቸው ታውቋል።

ታጣቂዎቹ የፀጥታ አካላት በማይኖሩበት ስፍራ ላይ አድፍጠው በመጠበቅ ግለሰቦቹን ይጓዙበት ከነበረ ተሽከርካሪ ላይ አስወርደው የገደሏቸው መሆኑንና ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዷ ሴት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ግዛቸው፣ ‹‹የግድያው ድርጊት እጅግ ጭካኔ የተሞላበትና በሰው ላይ የማይፈጸም›› ነው ብለዋል።

ኃላፊው ጨምረውም ግድያው የተፈጸመው ሦስቱ ግለሰቦች ከዞን ወደ ወረዳ እየተመለሱ ባሉበት ወቅት መሆኑን ያመለከቱ ሲሆን፣ ‹‹ሰዎቹ የአካባቢያቸውን ሕዝብ በማገልገል የሚታወቁና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ናቸው›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንዳሉት ግድያ የተፈጸመው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኛ ቡድንነት በተሰየመው ሸኔ በተባለው ታጣቂ ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።

ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ጦር የሚለውና ለጥቃቱ በአካባቢው ባለስልጣናት የተወነጀለው ቡድን ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ተርቢ በእንዲህ አይነት ድርጊቶች ውስጥ የቡድናቸው ታጣቂዎች እጅ እንደሌለበት አመልክተው፣ ሌሎች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ቡድናቸው እየተከሰሰ ነው ሲሉ ማስተባበላቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል፡፡

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግዛቸው ጋቢሳ በበኩላቸው ታጣቂዎቹ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በተወሰኑ ሰዎች ላይ ያተኮረ ሳይሆን በሁሉም የአካባቢው ነዋሪ ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ አስረጂ በማለትም ‹‹በአቡና ግንደ በረት ወረዳ ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ 3 ሰዎችን ገድለዋል። የመንግሥት አመራር ብቻ ሳይሆን በቀያቸው ያሉ ንጹህንን እና ትምህርት ቤት ያሉ ልጆችን›› መግደላቸውን ገልጸዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑን ከምዕራብ ሸዋ ዞን በማስወገድ የሕግ የበላይነት የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img