አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ኅዳር 12፣ 2014 ― በሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዐብዱልፈታህ አልቡርሃን በተካሄደባቸው መፈንቅለ መንግስት የተወገዱት ዐብደላ ሐምዶክ ወደ ቀደመ ሥልጣናቸው ሊመለሱ መሆኑ ተነግሯል።
መፈንቅለ መንግሥቱን አድርገው የዐብደላ ሐምዶክን የሲቪል አስተዳደር አስወግደው መሪዎቹን ያሰሩት ጦር አዛዡ፣ ዐብደላ ሐምዶክ ወደ ቀደመ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ መስማማታቸውን አሸማጋዮችን ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
መፈንቅለ መንግስት አድራጊው የሱዳን ጄነራል ከቀናት በፊት አዲስ ሉዓላዊ ምክር ቤት ማቋቋማቸው አይዘነጋም።
ቡርሃን ምክር ቤቱን ያቋቋሙት በመፈንቅለ መንግስቱ የፈረሰውን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ለመተካት በሚል ነበር፡፡
አዲስ የተመሰረተው ምክር ቤት 15 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱን ሲመሩት የነበሩት ቡርሃን ራሳቸውን የአዲሱ ምክር ቤት መሪ አድርገው ሾመዋል፡፡
አሁን ወደ ሥልጣናቸው ሊመለሱ ነው የተባሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ መፈንቅለ መንግስቱ ከተደረገ አንስቶ በቁም እስር ላይ መሆናቸው ይነገራል።