Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ይደራደራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 10 2014 ― የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶንዮ ብሊንክን የፌዴራል መንግስት እና ሕወሓት ለዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ይደራደራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ‹‹ሁለቱ ኃይሎች ልዩነታቸውን በንግግር ለመፍታት የተኩስ አቁም አድርገው ቁጭ ብለው በመነጋገር፤ ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን አረጋግጠው፤ ለዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ይደራደራሉ የሚል ተስፋ አለኝ›› ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን እንዲሁም ተሳትፎ አላቸው ባለቻቸው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ በባለስልጣናት ላይ ማእቀብ የጣለችው አሜሪካ፣ ጉዳዩን ለመፍታት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና መልእክተኛዋ ጄፍሪ ፌልትማንን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ልካለች፡፡

አዲስ አበባ የሚገኙት ፌልትማን፣ በትላንትናው እለት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው ጦርነቱን መግታት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እና ፌልትማን ያደረጉት ውይይት ይዘት ዝርዝር መረጃ ይፋ ባይደረግም፣ ሬውተርስ የዜና ወኪል የተኩስ አቁም ላይ መድረስን ጨምሮ ሌሎችም ጦርነቱን ማቆም ስለሚቻልባቸው መንገዶች መነጋገራቸውን ዘግቧል።

በተመሳሳይ የሽምግልና እንቅስቃሴ እያከናወኑ የሚገኙት የአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አዲስ አበባ መግባታውን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አሳውቋል፡፡ ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመገናኘት፣ ‹‹የሰላም መፍትሔ በማፈላለግ ሂደታቸው የደረሱበትን ሐሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያብራሩና በሰብአዊ ርዳታ ዙሪያ እንደሚወያዩ›› እንደሚጠበቅ የኮሚኒኬሽን አገልግሎቱ ገልጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኦባሳንጆ በዚሁ ቆይታቸው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ ኅብረት አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ጉዳይ እስካሁን በደረሱባቸው ነጥቦች ዙሪያ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ነው የተገለጸው፡፡

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ከዚህ ቀደም የፌዴራል መንግስት እና ሕወሓት መሪዎችን ካነጋገሩ በኋላ የማደራደር ጥረቴን አልቀበልም ያለ አካል የለም ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img