አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 8፣ 2014 ― በሱዳን መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ሥልጣን የተረከበውን ወታደራዊ አገዛዝ በመቃወም በትላንትናው እለት በተካሄደ ሰልፍ 15 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
የሱዳን ሐኪሞች ማእከላዊ ኮሚቴ እንደገለጸው ከሆነ፣ ከሟቾቹ መካከል 14 ሰዎች የተገደሉት በመዲናዋ ካርቱም ሲሆን፣ አንደኛው በኡምዱርማን ነው፡፡
ትላንት በተካሄደው ተቃውሞ የጸጥታ አካላት በሰልፈኞቹ ላይ ጥይት መተኮሳቸውን እንዲሁም፣ አስለቃሽ ጭስ እንደተጠቀሙ የሱዳን ትሪቡን ዘገባ ያመለክታል፡፡
የሱዳን ሐኪሞች ማእከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መረጃ ከሞቱት 15 ሰዎች ሌላ ወደ 80 ገደማ ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ከቆሰሉት መካከል በርካቶቹ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን ባለፈው ወር በመሩት መፈንቅለ መንግስት የሲቪል አስተዳደሩን ማስወገዳቸው ይታወሳል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የሲቪል አስተዳደሩ እንዲመለስ የሚጠይቁ ሰልፈኞች በተደጋጋሚ በአገሪቱ ጎዳናዎች ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
ተቃውሞ አድራጊዎቹ ከሰሞኑ ሲያስተባብሩት የነበረውን ሰልፍ ለመስተጓጎል የመንግስት አካላት ቀድሞ ካደረጉት በተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔትን ማቋረጥ፣ በትላንትናው እለት ደግሞ አጠቃላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ማቋረጥ መሸጋገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ መፈንቅለ መንግስቱን ያደረጉት አል ቡርሃን፣ ከሰሞኑ የሽግግር አስተዳደር መስርተው ራሳቸውን መሪ አድርገው ሾመዋል፡፡
በጦር አዛዡ የተወገደው የሲቪል አስተዳደሩን ይመሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብደላ ሐምዶክ፣አሁንም ድረስ በቤት ውስጥ በየቁም እስር እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ አል ቡርሃን ግን ከሥልጣን ያስወገዷቸው ዐብደላ ሐምዶክን ጨምሮ ሌሎችም ከሰሞኑ ከእስራ ነጻ እንደሚደረጉ አገራቸው ለተገኙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ መናገራቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የአፍሪካ አህጉር መሪ ድርጅት የሆነው የአፍሪካ ኀብረት አገሪቱን ማገዱ ይታወቃል፡፡