አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 7፣ 2014 ― በመስከረም ወር መገባደጃ በአዲስ አበባ ከተማ ጀሞ ሚካኤል በሚባል አካባቢ አንዲት እናትን በልጇ ፊት ዘግናኝ ድብደባ የፈጸሙት ሁለት የፖሊስ አባላት ከሥራ መባረራቸው ተሰምቷል፡፡
በወቅቱ ሰሚራ በተባለችው የልጅ እናት ላይ ድብደባው ሲፈጸም የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች መሰራጨቱን ተከትሎ ነበር ፖሊሶቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡
የፖሊሶቹን ጉዳይ የያዘው የንፋስ ስልክ ላፍቶ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፖሊስ አባላቱ ለፈጸሙት ድርጊት እያንዳንዳቸው በ3 ሺሕ 300 ብር እንዲቀጡ መወሰኑ የተነገረ ሲሆን፣ ሆኖም የተሰጠው ፍርድ በቂ አይደለም ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለሌሎች ፖሊሶች ማስተማሪያ እንዲሆን በማለት ሁለቱንም ፖሊሶች ከሥራ ማባረሩን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ መናገራቸውን ቁም ነገር ሚዲያ ኢትዮ ኤፍ ኤምን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ በ171 የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች ከሥነ ምግባር ውጭ በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት አቤቱታ እንደቀረበባቸው የተነገረ ሲሆን፣ 29 ያህሉ በከፍተኛ የሥነ ምግባር ችግር ከስራ መባረራቸው ታውቋል፡፡