Friday, November 22, 2024
spot_img

የአውሮፓ ኅብረት ሹሙ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ አካላት ጦርነቱን አቁመው የንግግር በር እንዲከፍቱ በድጋሚ ጠየቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 6 2014 ― የአውሮፓ ኅብረት የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ አካላት ጦርነቱን አቁመው ለንግግር እድል እንዲሰጡ በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡

ይህ የቦሬል አስተያየት የመጣው ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ የነበሩት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እየሠሩበት የሚገኘውን የፌዴራል መንግስት እና ሕወሓትን የማሸማገል እንቅስቃሴ በተመለከተ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ኦባሳንጆ በመግለጫቸው ከመንግስትም ሆነ በመንግስት ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀው ሕወሃት በኩል የሰላም ፍላጎት መኖሩን በመግለጽ፣ ሰላም በሚመጣበት መንገድ ላይ ግን ልዩነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛው ለሚካሄዱት የማሸማገል እንቅስቃሴ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡ የጠቀሱት የአውሮፓ ኅብረት የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊው ቦሬል፣ በኢትዮጵያ ተፋላሚ አካላት ከቃላት በዘለለ ወደ ተግባር በመግባት ጦርነቱን አቁመው ለንግግር እድል እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ሲያወጣ የሰነበተው የአውሮፓ ኅብረት፣ እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ለውጥ ከሌለ ከማእቀብ ጋር የተያያዙ አጀንዳዎችን እንደሚያጤን ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡

የማሸማገል እንቅስቃሴያቸው በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ የተቸረው ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የፌዴራል መንግስት ባለሥልጣናትን እንዲሁም የሕወሓት አመራሮችን ከማግኘታቸው በተጨማሪ፣ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳዳር ሺመልስ ዐብዲሳን ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የአፋር ክልል አመራሮችን የማግኘት እቅዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ይህ የማሸማገል ስራ እንዲሳካ ቁርጠኛ እንደሆኑ የገለጹት ኦባሳንጆ፤ የኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን መሪዎችን ማግኘታቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img