አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 2፣ 2014 ― የሱዳን ዋናው የሲቪል ፓለቲካዊ ጥምረት ከወታደራዊ ኃይሉ ጋር የሚያደረገውን ድርድር ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ጥምረቱ በሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሀን ከተመራው የጥቅምት 25፣ 2014 መፈንቅለ መንግስት በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከወታደራዊ ኃይሉ ጋር የሚደረገውን ድርድር ተቀባይነት የለውም ማለቱን የአል ዐይን ዘገባ ያመለክታል፡፡
በቤት ውስጥ እስር ላይ የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክን እንደሚደግፍ የገለጸው ጥምረቱ፣ ሁሉም ነገር ከመፈንቅለ መንግስት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ መጠየቁም ነው የተነገረው፡፡
መፈንቅለ መንግስቱ የተካሄደው ሲቪሎች ባነሷቸው ኋላም ወደ ጠረጴዛ በመጡ ጥያቄዎች እንደነበር ያስታወሱት የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች ቃል አቀባይ፣ ‹‹አጋርነቱን አላፈረስንም፤ ወደ ህገ መንግስታዊ ሰነዶች መለስ ብለን መመልከት ይኖርብናል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም የጦሩ አዛዥ አል ቡርሃን ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት የነበራቸውን ‹‹የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድርነት ስልጣን›› ጥምረቱ አይቀበልም ብለዋል፡፡
ከሱዳን ሲቪል ጥምረት ተቃውሞ ያስተናገዱት አል ቡርሃን በሱዳን ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር እውን እንዲሆን እንዲሁም በፈረንጆቹ ሐምሌ 2023 የተሳካ ምርጫ ለማካሄድ እንደሚሰሩ መናገራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
አል ቡርሃን ከቀናት በፊት በቀጣይ በአገሪቱ ይመሠረታል የተባለው አዲስ መንግስት ጉዳይ እንዲፋጠን ከአሜሪካ ጋር መስማማታቸውም ተገልጾ ነበር፡፡