አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 29፣ 2014 ― በትላንትናው እለት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ጋር መቐለ የነበሩት የአፍሪካ ኅብረት ለምሥራቅ ልዩ መልእክተኛ አድርጎ የሰየማቸው ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ ለኅብረቱ የጸጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገለጻ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡
ኦባሳንጆ ገለጻ ባደረጉበት በዛሬው የጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የኅብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ፣ በአፍሪካ ኅብረት የግብጽ ቋሚ ተወካይ መሐመድ ጋድ እና በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ መሳተፋቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ መልእክተኛው ገለጻውን ያደረጉት ትላንት ወደ ትግራይ አቅንተው ሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የኦባሳንጆን የመቐለ ጉዞ በተመለከተ የሕወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ ኦባሳንጆ እና ማርቲን ግሪፊትስ ከደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል ጋር መገናኘታቸውን አረጋግጠው፣ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ በምን ጉዳይ እንደተወያዩ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
በመንግሥት በኩል እስካሁን ድረስ የኦባሳንጆን ጉዞ በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም፣ ሐሙስ ጥቅምት 25፣ 2014 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የአፍሪካ ቀንድ ተዋካይ ምን ዓይነት መፍትሔ ይዘው እንደሚመጡ መንግሥት እየጠበቀ ነው ብለው ነበር፡፡
ሕወሓት በአገር ላይ ጦርነት ከከፈተ በፊትም ሆነ በኋላ ‹‹ወርቃማ›› ዕድሎችን እንዳጠፋ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከጅምሩ በሠለጠነ መንገድ መፈታት ይችል እንደነበር ገልጸው፣ ጦርነት ከገባ በኋላም ቀርቦለት የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣሱ ያልተፈለገ ውድመት ስለመድረሱ ለዲፕሎማቶች አስረድተዋል፡፡
የጦርነቱን መቀጠል ዓይተው መፍትሔ ለማፈላለግ የሞከሩትን እንደ ኬንያና ደቡብ ሱዳን የመሳሰሉ የጎረቤት አገሮች ምሥጋና ያቀረቡት ሬድዋን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አሁንም ለእንዲህ ዓይነት የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርቡ አገሮችን ምንጊዜም በቀና እንደሚቀበል አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ መጀመርያ መፍትሔ መሆን ያለበት ሕወሓት የሚያደርገውን ወረራ እንዲያቆም ማሳሰብ ይጠብቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰበሰብ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በተመሳሳይ ለሌላ ጊዜ አስተላልፎት የነበረው ኢትዮጵያን የተመለከተ ውይይትም በዛሬው ዕለት ይካሄዳል ተብሎ ተጠብቋል፡፡