አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 25፣ 2014 ― የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን በዛሬው እለት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ልዩ መልዕክተኛው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኃላ ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕመት ፈቂ ጋር ተገናኝተው መክረዋል። ይህንኑ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት ፈቂ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። እንደ ሊቀመንበሩ ሁለቱ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ እና ሱዳን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረዋል።
በዛሬው እለት አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ መልዕክተኛ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ የሚቆዩት ለሁለት ቀናት ነው።
ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ተብብሶ ለቀጠለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መላ ለመፈለግ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ከሕወሃት ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ጦርነት አንድ አመት የደፈነ ሲሆን፣ የሰሞኑን ውጊያ ተከትሎ በመላው አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በዛሬው እለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል።
ከ10 ቀናት በፊት ሱዳን የነበሩት ፌልትማን፣ ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።