Tuesday, November 26, 2024
spot_img

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሕወሓት በኮምቦልቻ ከ100 በላይ ወጣቶች ጨፍጭፏል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 22፣ 2014 ― በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ሀይል በኮምቦልቻ ከተማ ሰርጎ በመግባት ከ100 በላይ የከተማዋን ወጣቶችን አሰልፎ ጨፍጭፏል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሕወሓት በኮምቦልቻ ወጣቶቹ ላይ ጭፍጨፋውን ፈጽሟል የተባለው ትላንት ሌሊቱን ሰርጎ በመግባት ነው፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የግል እና የመንግስት ሀብቶችን እየዘረፉ እና እያወደመ ነው ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል በቦርከና ዳዋ ጨፌ አካባቢዎች ሕወሓት እየመጣ ነው በሚል ሌላኛው በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው በመንግስት ሸኔ የሚባለው ኃይል ‹‹መንገድ የመዝጋት እና ሌሎች አፍራሽ ድርጊቶችን ለመፈፀም ቢሞክርም በአካባቢው ወጣቶችና በጀግናው መከላከያ ሰራዊት አላማው ከሽፎበታል›› ብለዋል።

ኃላፊው የአገር መከላከያ ሰራዊት በክህደት ተፈጥሮበታል ያሉትን የውጊያ መዛነፎች ‹‹እንደገና በማስተካከል አሁንም ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ይገኛል›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡  

አያይዘውም ‹‹መንግስት ተዳክሟል፣ ሕወሀት አሸንፎ እየመጣ ነው›› በሚል ደሴ ላይ እንደተፈፀመው ሁሉ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ጭፈራ የገቡ ኃይሎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም አሳስበዋል። ይህን አስመልክቶ መንግስት እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ መግለጫ የመጣው የሕወሓት ኃይሎች የአመራ ክልል ከተማ የሆነችው ኮምቦልቻን ተቆጣጥረናል ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ጭፍጨፋውን በማድረስ በመንግስት ክስ የቀረበበት ሕወሓት የሰጠው ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img