Sunday, September 22, 2024
spot_img

አሜሪካ በኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ አካላት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለተኩስ አቁም እንዲደራደሩ አሳሰበች

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 22 2014 ― የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን የምትሰጠው አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊዋ አንቶንዮ ብሊንከን በኩል በኢትዮጵያ የጦርነቱ ተፋላሚ አካላት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለተኩስ አቁም እንዲደራደሩ አሳስባለች፡፡

አንቶንዮ ብሊንከን በዛሬ እለት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ማስታወሻ የሕወሓት ኃይሎች ደሴ እና ኮምቦልቻን ይዘዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን አሳሳቢ ነው ብለውታል፡፡

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊው አክለውም ውጊያው መቀጠሉን በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ ቀውሱን የሚያባብስ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው ሳምንት አንድ ዓመት የሚሞላው በትግራይ ክልል ጀምሮ፣ ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ኃይሎች ጦርነት ከሰሞኑ በስፋት መቀጠሉን መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

በውጊያው የሕወሓት ኃይሎች ኮምቦልቻን መቆጠጣራቸውን በቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ በኩል ቢናገሩም ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

የሕወሃት ኃይሎች በተመሳሳይ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 20፣ 2014 ደሴ ከተማን መቆጣጠራቸውን ቢያሳውቁም መንግስት አስተባብሎ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አሜሪካ በቃለ አቀባይዋ ኔድ ፕራይስ በኩል ቡድኑ ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲገታና እንዲሁም ከአማራና አፋር ክልሎችም እንዲወጣ ጠይቃ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሕወሃት በከተሞች ላይ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እንዳይጠቀም ከማሳሰብ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መከላከያ በመቀሌ እና በተለያዩ የትግራይ ክልሎች የሚያደርገውንና ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነውን የአየር ጥቃትም ማቆም አለበት ብላለች።

እነዚህ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መግለጫ ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ የክት ጉዳዩን አቆይቶ ሕወሓትን ‹ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ማናቸውንም መሳሪያ እና አቅም ይዞ በሕጋዊ አደረጃጀት መዝበት አለበት›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የመረረውን ትግል ታግለን፣ ጣፋጩን ድል እናጣጥማለን›› ባሉበት መግለጫ፣ ‹‹ሕወሓት በአራት ግንባሮች ተኩስ ከፍቶ አገር የማፍረስ ተግባሩን ገፍቶበታል›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ሰሞኑን ያለ የሌለ ኃይሉን ወደ ወሎ ግንባር አምጥቷል። አገር ለማጥፋት የመጣ መንጋ አገር ለማዳን የተነሣን ኃይል ይረብሸው ይሆናል፣ ሊያሸንፈው ግን አይችልም›› ሲሉም አስፍረዋል፡፡

በተመሳሳይ ጦርነቱ እየተካሄደበት የሚገኘው የአማራ ክልላዊ መንግስት በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን አቋርጠው በጀትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለጦርነት እንዲያውሉ መወሰኑን ትላንት ምሽት አስታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img