Monday, September 23, 2024
spot_img

የአማራ ክልል ተቋማት መደበኛ አገልግሎታቸውን አቋርጠው በጀትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለዘመቻ እንዲያውሉ መወሰኑን አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ጥቅምት 21፣ 2014 ― የአማራ ክልላዊ መንግስት በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን አቋርጠው በጀትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለጦርነት እንዲያውሉ መወሰኑን ያስታወቀው በዛሬው እለት ባወጣው አስቸኳይ ጥሪ ነው።

የክልሉ መንግሥት ባወጣው ዘጠኝ ነጥቦችን በያዘው መግለጫ “አሸባሪና ወራሪ” ያለው የሕወሃት ኃይል በክልሉ ሕዝቦች ላይ “መጠነ ሰፊ ጥቃት እየፈፀመ ህዝቡን እየገደለና እያዋረደ፤ ንብረቱን እየዘረፈ፣ እያወደመ እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ነው” ብሏል።

በመሆኑም “በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ብቻ ማሸነፍ የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ” ውሳኔዎቹን ማሳለፉን ነው የገለፀው።

የክልሉ መንግስት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት አቋርጠው በጀትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለጦርነት እንዲውል ከመወሰኑ በተጨማሪ፣ ሁሉም የመንግስት ተሸከርካሪ ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ ለዘመቻ አገልግሎት እንዲውል እንዲደረግ፣ የግል ተሸከርካሪ ባለቤቶች ለዘመቻው ስኬት ሲባል በተፈለገ ጊዜ ሁሉ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመስጠት ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ፣ በየደረጃው የሚገኝ አመራር የሕልውና ያለውን ዘመቻ ተቀብሎ የሚሰለፈውን ሕዝብ አደራጅቶ ከፊት ሆኖ እየመራ ወደ ግንባር እንዲዘምት ያለ ሲሆን፣ ይህን በማያደርጉ አመራሮች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ብሏል።

በተጨማሪም የመንግስትና የግል የጦር መሳሪያ የታጠቀ በሙሉ ለዘመቻው አገልግሎት እንዲውል፣ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛዉም የግል መሳሪያ የታጠቀ የክልሉ ነዋሪ በማንኛውም ምክንያት በዘመቻው ላይ የማይሳተፍ ከሆነ የታጠቀውን የግል መሳሪያ በአደራ ለመንግስት እንዲያስረክብ ወይም እድሜው ለትግል ለደረሰ እና አካላዊ ጤንነት ላለው ለቤተሰብ አባሉ ወይም ለሌላ ሰው በማስተላለፍ ለህልውና ዘመቻዉ አገልግሎት እንዲውል፣ ዘመቻውን ከተቀበሉት ውጭ ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ “በየአካባቢው ተደራጅቶ የአካባቢውን ጸጥታ እንዲጠብቅ፣ ጸጉረ ልውጦችንና ሰርጎ ገቦችን እንዲከታተልና ለሕግ አስከባሪ አካላት አሳልፎ እንዲሰጥና ለሕልውና ዘመቻው የበኩሉን ኃላፊነት ሁሉ እንዲወጣ እና ዘመቻው ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ለትግሉ በተለያየ መንገድ እንቅፋት በሚሆን ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን ላይ በየደረጃዉ እየተወሰነ የጸጥታ አካሉ አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወስድ ነው የወሰነው።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸዉ ተቋማት ዉጭ በሁሉም ከተሞች ከምሽቱ 2 በኋላ እንቅስቃሴ እንደማይቻልም አስታውቋል።

በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች ክልሎች በገፋው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሃት ኃይሎች ጦርነት ከሰሞኑ በደሴ አካባቢ ተጠናክሮ መቀጠሉ ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል።

በቀጠለው ጦርነት የሕወሃት ኃይሎች ኮምቦልቻን ተቆጣጥረናል ሲሉ በቃል አቀባያቸው ጌታቸው ረዳ በኩል ቢያሳውቁም፣ በመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img