አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 19፣ 2014 ― ኃይሌ ጋርመንት ሰፈራ በተባለው አካባቢ በሚገኘው ሀና ማርያም የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የምግብ መበከል በሚመስል መልኩ በርካታ ተማሪዎች ታመው ወደ ሕክምና ተቋማት እየተወሰዱ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 1 ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አረጋግጫለሁ ብሎ ዘግቧል።
የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ባለሞያ የሆኑት ኢየሩሳሌም አንዱዓለም እንዳሉት ከረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ተማሪዎቹ ያጋጠማቸውን ህመም በተመለከተ መረጃው ለወረዳው ተላልፏል። ይህንኑ ተከትሎ በተቻለ ፍጥነት ህክምና እንዲያገኙ በአቅራቢያው ወደሚገኙ የጤና ተቋማት ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አምቡላንሶች የታመሙትን ተማሪዎች ወደተለያዩ ተቋማት መወሰዳቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች መስማቱንም ዘገባው አመልክቷል።
የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አያይዘውም ችግሩ በምን ምክንያት እንደተፈጠረ ህክምናው እስኪያረጋግጥ ድረስ ከተዛቡ መረጃዎች መጠበቅ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ የተጎዱት ተማሪዎች ብዛት እና ያሉበት ሁኔታ በደንብ ከተጣራ በኋላ ይፋ ይደረጋል ማለታቸው ተመላክቷል።
ተፈጥሯል በተባለው የምግብ መበከል ሰበብ የከፋ ጉዳት ያስተናገደ ተማሪ ስለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም።