Monday, November 25, 2024
spot_img

አውሎ ሚዲያ በመንግሥት ተፈጸመብኛል ባለው በደል ሰበብ ሠራተኞቹን መበተኑን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 18፣ 2014 ― በበይነ መረብ ዜና እና ትንታኔዎችን ሲያቀርብ የቆየው አውሎ ሚዲያ በመንግሥት ተፈጽሞብኛል ባለው በደል ሰበብ ሠራተኞቹን መበተኑን አስታውቋል።

አውሎ ሚዲያ ሴንተር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባስነበበው መግለጫ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሚዲያ ዘርፍ ላይ በመሰማራት በርካታ የሚዲያ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሷል።

ያስታወሰው ሚዲያው፣ ፡፡ በተለይ ሀገራችን ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስብስብና ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ገንቢ ሚና በመያዝ በተለይም የተራራቁ ፅንፍ ሃሳቦችን በማቀራረብና ብሎም እኩል ድምፅ በመስጠት

ነገር ግን ከባለፈው ዓመት ሰኔ 23 ጀምሮ መንግስት የፌዴራል ፖሊሲን በመላክ በርካታ የድርጅቱን ንብረቶች ከመውሰዱም በላይ የስራ ቦታውን ሙሉ በሙሉ አሽጎብኛል ያለው አውሎ ሚዲያ፣ የድርጅቱን ሰራተኞችም “ኢ ፍትሃዊ” ሲል በገለፀው መንገድ አፋር ክልል አዋሽ ሰባት የፈዴራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ በማሰርና በማፈን ከፍተኛ ግፍ እንደፈፀመባቸው አመልክቷል።

እነዚሁ የሰብአዊ መብት ተቋማት አድርገውታል ባለው ጥረት ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ፍርድ ቤቱም እንዲለቀቁ በመወሰኑ ከበርካታ እንግልትና ስቃይ በኋላ መለቀቃቸውን ገልጿል።

ሆኖም የፍትሕ ተቋማቱ የድርጅቱን ሰራተኞች እንዲለቀቁን ብሎም የድርጅቱም ሆነ የሰራተኞቹ የግል ንብረት እንዲመለስና ፖሊስ ያሸገው የድርጅቱ ቢሮ እንዲከፈት ቢወስኑም እስካሁን ድረስ ከፌዴራል ፖሊስ ይህ ነው የሚባል ህጋዊ መልስና ተግባር ሊገኝ አልተቻለም ነው ያለው።

አውሎ ሚዲያ ያሉትን ሰራተኞች ህጋዊ ቅጥራቸውን በማስቀጠል እስከ ዛሬ ድረስ ከመንግስት ተቋማት መፍትሄ እየጠየቀ መቆየቱን አስታውሶ፣ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ማለትም የፌዴራል ፖሊስ ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እና የሚመለከታቸው ተቋማትና ሃላፊዎች “ይህ ነው የሚባል ህጋው መፍትሄም ሆነ እርምጃ ሊሰጡን አልቻሉም” ሲል ሁኔታውን አሳዛኝ ብሎታል።

በመሆኑም የሚዲያ ድርጅቱ በመንግስት ተፈጥሯል ባለው “”ችግር” ምክንያት ሰራተኞችን ሙሉ በሙሉ ማሰናበቴን እወቁት ብሏል።

የሚዲያ ድርጅቱ በማጠቃለያው አሁንም ኢ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመንግስት ተወስዶብኛል ያላቸውን ንብረቶች እንዲመለስ፣ ቢሮውም እንዲከፈትለት እንዲሁም መንግሰት የሚዲያ ምህዳሩን እጅግ ከሚያጠቡና ከሚያቀጨጩ ተግባራት በመቆጠብ በዘርፉ ያሳየውን መጠነኛ ነፃነት ከመጥፋት እንዲታደገው ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img