Thursday, November 21, 2024
spot_img

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ባለቤታቸው ከእስር መለቀቃቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 17 2014 ― ከትላንት በስትያ ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 በአገሪቱ ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር በአገሪቱ ሲቪል አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡

ቀድሞ በወጡ መረጃዎች በዚህ መፈንቅለ መንግሥት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዐብደላ ሐምዶክ ከስልጣናቸው ተነስተው ባልታወቀ ስፍራ መታሰራቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡ ኋላም በትላንትናው እለት አል ቡርሃን መገናኛ ብዙኃን ፊት ቀርበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔ ቤት ይገኛሉ ብለው ነበር፡፡

አልጀዚራ ይዞት በወጣው መረጃ ደግሞ ሐምዶክ በአሁኑ ወቅት ከባለቤታቸው ጋር ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰው በከፍተኛ ጥበቃ ውስጥ እንደሚገኙ አስነብቧል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቤታቸው የመመለስ ዜና የመጣው መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ በሶዳን ጦር ላይ በርካታ ተቃውሞ መበርከቱን ተከትሎ ነው፡፡

የዐብደላ ሐምዶክ ከእስር መለቀቀቅ ቢሰማም፣ መፈንቅለ መንግስት በተካሄደበት ወቅት የታሰሩ ሰባት የሲቪል አስተዳዳሩ ባለሥልጣናት ግን አሁንም ታስረው እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡ በወቅቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሐምዛ ባሉል፣ የዐብደላ ሐምዶክ የሚዲያ አማካሪ ፈይሰል መሐመድ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ኢብራሂም አል ሸይኽ፣ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ቃል አቀባይ መሐመድ አል ፈቂ እና የካርቱም አስተዳዳሪ አይመን ካሊድ ይገኙበታል፡፡

የሱዳን ጦር መፈንቅለ መንግስቱን ያደረገው በአገሪቱ አንዣቧል ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቀረት መሆኑን አስታውቋል፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ አሜሪካ ለአገሪቱ የምትሰጠውን 700 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ያገደች ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረትም ተመሳሳይ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቋል፡፡ ሁለቱ አካላት የሲቪል አስተዳደሩ ወደ ስልጣኑ እዲመለስ ጠይቀዋል፡፡

የሲቪል አስተዳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል መባሉን ተከትሎ እርዳታ አግጃለሁ ያለችው አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሐምዶክን በስልክ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ አሁንም በእስር ላይ ያሉ ሌሎች የሲቪል አስተዳደር አመራሮች እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡

ሰኞ እለት በሱዳን በተደረገው መፈንቅለ መንግስት ባስከተለው ሕዝባዊ ተቃውሞ እስከ ሰባት የሚሆኑ ሲቪል ዜጎች መገደላቸውን ሪፖርቶች ያመለክተሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ለእስርት ዓመታት ሱዳንን የመሩት ዑመር አል በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በአገሪቱ ስልጣኑን የተጋሩት የሲቪል እና የወታደሩ መሪዎች መካከል ቅሬኔ መኖሩ በተደጋጋሚ ሲገለጽ መቆየጡ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img