Monday, September 23, 2024
spot_img

በምዕራብ ኦሮሚያ ለሳምንታት ታግተው ነበር የተባሉ አራት የቱሉ ኬፒ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ሠራተኞች መለቀቃቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 16 2014 በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የቱሉ ኬፒ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ፕሮጀክት ኩባንያ ለሳምንታት ታግተው ቆይተዋል የተባሉ አራት ሠራተኞች መለቀቃቸው ተነግሯል፡፡

የኩባንያው ሠራተኞች ታግተው ነበር የተባሉት በመሰከረም ወር አጋማሽ ላይ ሲሆን፣ እገታውን የፈፀሙ አካላት ማንነት እስካሁን ድረስ ይፋ አለመሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ የዜና ተቋሙ ከአራቱ ታጋቾች መካከል የውጭ አገር ዜጋ መኖሩን መረጃ አግኝቻለሁ ቢልም፣ ኩባንያው ‹‹ሠራተኞቹን በእኩል የሚመለከት በመሆኑ በዜግነታቸው ለመለየት ፍላጎት የለውም›› በማለት ዝርዝር ከመስጠት እንደተቆጠበ ተገልጧል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ‹‹ሸኔ›› የሚለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ስለ እገታው የማውቀው ነገር የለም ማለቱም ተመላክቷል፡፡ የኩባንያው ሠራተኞች በአካባቢው በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በእገታው ምክንያት ድርጅቱ ከመስከረም 19፣ 2014 አንስቶ በጊዜያዊነት ሥራውን ለማቋረጥ ተገድዶ ነበር።

 ኩባንያው ከሠራተኞቹ መለቀቅ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ግለሰቦቹ የታገቱት ለማዕድን ማውጫው ፕሮጀክት የሚያገለግሉ የትራንስፖርት መስመሮችን በመለየት ላይ ሳሉ ነበር። ስለ ታጋቾቹ ዜግነት እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ለሠራተኞቹና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሲባል ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን፣ ከእገታው ነጻ ሲወጡ ምንም ችግር ሳይገጥማቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸው ተጠቅሷል።

ኩባንያው ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ግን ካለፈው መስከረም ጀምሮ ታግተው የነበሩት አራት ሠራተኞቹ እና ኮንትራክተሮች ‹‹ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በደህና ሁኔታ›› መለቀቃቸውን ገልጿል።

ነገር ግን ድርጅቱ ስለግለሰቦቹ ዜግነት፣ በእገታው ስር አውሏቸው ስለቆየው ወገን እና ስለተለቀቁበት ሁኔታ ከመግለጽ ተቆጥቧል። ከዚህ ቀደም በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ እንደሚቀሳቀስ የሚነገረው የሸኔ ታጣቂዎች ሁለት ለማዕድን አውጪ ድርጅት ይሰራሉ ያሏቸውን የአፍጋኒስታን ዜጎችን በመነሲቡ ወረዳ ማገታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ኦሮሚያ ለማዕድን አውጪ ድርጅት ይሰሩ የነበሩ ሶስት ቻይናውያን በቡድኑ ከታገቱ በኋላ ለዓለም አቀፉ ኩባንያ መሰጠታቸውን መነገሩም ይታወሳል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img